Monday, October 19, 2015

“ልበ ነጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና” (ማቴ. 5፥8)

ከደምፀ ቃለ አብ

ጌታችን አየሱስ ክርስቶስ በተራራው ላይ ያስተማራቸው ትምህርቶች ደስታ ለሞላበት አኗኗር መሠረት ናቸው፡፡ ትምህርቶቹ በተራራ ላይ የተሰበኩ ሲሆኑ የመንፈሳዊ ከፍታም መገለጫዎች ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግ ምትሐታዊ ቊጥሮች የምስጢር ቊልፎች የሉም፡፡ የመንፈሳዊ ከፍታ መመዘኛው የተራራው ስብከት ነው፡፡ የተራራው ስብከት የውስጥ መጠይቅ በመሆኑ ሰው ራሱን የሚያይበትና የሚያስውብበት ልዩ ክፍል ነው፡፡ በተራራው ስብከት ዓለም ትልቅ ስፍራ የምትሰጣቸው ነገሮች ውድቅ ሆነዋል፡፡ ዓለም፡-
*     ራስህን አክብር ትላለች፤ የተራራው ስብከት ደግሞ፡- በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው$ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና (ማቴ. 5፥3) ይላል፡፡ የዓለም ስብከት ደግሞ ራስህን አክብር፤ ዓለም ያንተ ናትና የሚል ይመስላል፡፡
*     ደስተኛ ብቻ ሁን ትላላች፤ የተራራው ስብከት ደግሞ፡- የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው$ መጽናናትን ያገኛሉና፥ማቴ. 5$4) ይላል፡፡ የዓለም ስብከት ደግሞ፡- ደስተኛ ብቻ ሁን፤ ስለ ሌላው ምን አገባህ ትላለች፡፡
*     በደልን አትርሳ ትላለች፡፡ የተራራው ስብከት ደግሞ፡- የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና (ማቴ. 5፥5) ይላል፡፡ የዓለም ስብከት ደግሞ፡- በደልን አትርሳ፤ አጥምደህ ያዘው፤ ላንተ ይገዛልና ትላላች፡፡
*     እንደ ጊዜው ኑር ትላለች፡፡ የተራራው ስብከት ደግሞ፡- ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና (ማቴ. 5፥6) ይላል፡፡ የዓለም ስብከት ደግሞ፡- ተመሳስለህ ኑር፤ ከሁሉም ትጠቀማለህ ትላለች፡፡
*     ተቀበል እንጂ የአንተን አታካፍል ትላለች፡፡ የተራራው ስብከት ደግሞ፡- “የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና” (ማቴ. 5፥7) ይላል፡፡ የዓለም ስብከት ግን፡- “አጠራቅም ይበዛልሃል” የሚል ነው፡፡
*     ንጽሕናህን ጠብቅ ትላለች፡፡ የተራራው ስብከት ደግሞ፡- ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና” (ማቴ. 58) ይላል፡፡ የዓለም ስብከት ግን፡- “ውስጥህን ማንም አያውቅም፤ ውጫዊ ንጽሕናህን ጠብቅ” ይላል፡፡

የሰው ልጅ ሲፈጠር እንዲኖረው የታቀደለት አኗኗር በተራራው ስብከት ውስጥ ተገልጾአል፡፡ እውነተኛ መልካምነትም ውጫዊ ማስመሰል ሳይሆን ውስጣዊ ታማኝነት መሆኑን የተራራው ስብከት ያስገነዝበናል፡፡ የተራራው ስብከት ርካታ ላጣው ለሰው አኗኗር ደስታን፥ ሁከት ለሚንጣት ዓለም ሰላምን የሚያመጣ ነው፡፡ የሰው ልጆች ለመዝናኛ የሚያውሉት ወጪ ከፍተኛ ነው፡፡ የዓለም መንግሥታት ለደኅንነትና ለመከላከያ የሚመድቡት በጀት ከፍተኛ ነው፡፡ የተራራው ስብከት በተግባር ላይ ቢውል ግን የዓለም ወጪ እንኳ ይቀንስ ነበር፡፡ በከፍተኛ ወጪዎች ግለ ሰቦች ርካታን ዓለምም አስተማማኝ ሰላምን አላገኙም፡፡ የተራራው ስብከት ግን የዓለም ሰላም መሠረት ነው፡፡

ጌታችን በተራራው ስብከት በአንቀጸ ብፁዓን በስድስተኛው ዘርፍ ላይ የተናገረው$ “ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው$ እግዚአብሔርን ያዩታልና” (ማቴ. 58) የሚል ነው፡፡ ዓለም ሁሉ የሚጨነቀው ስለ ውጫዊ ንጽሕና ወይም ስለ ፕሮቶኮል ነው፡፡ በዛሬው ዘመንም ራሳቸውን የሚጠብቁ ነገር ግን ራሳቸውን የማይጠይቁ ብዙ ትውልዶችን እያየን ነው፡፡ የአለባበስ ድምቀት የጎዳና ላይ የልብስ፥ የአላባበስ) ውድድር፣ የጌጥ ብዛትም እኔን ብቻ እዩኝ የሚል ይመስላል፡፡ ሰዎች ሰፊ ጊዜያቸውን፣ ብዙ ገንዘባቸውን የሚያጠፉት ለውጫዊ ንጽሕና ነው፡፡ ብዙ ጊዜአችንንና ገንዘባችንን የመደብንለት ነገር ሁሉ “የምንኖርለት” ነገር ነው፡፡ ጌታችን ግን ስለ ልብስ ሳይሆን ስለ ልብ ንጽሕና እየጠየቀን ነው፡፡ ዛሬ እያንዳንዳችንን “ልብህ ንጹሕ ነው ወይ፤” ብሎ ቢጠይቀን ምን እንመልስ ይሆን፤ በተቃራኒው ልብስህ ንጹሕ ነው ወይ፤ ቢለን ለመመለስ እንሽቀዳደማለን፡፡ የልብ አምላክ ግን የሚጠይቀው ልብን ነው፡፡

ቅዱስ መጽሐፋችን “ልብ” ብሎ ሲናገር ሥጋዊውን ሥራ ስለሚሠራውና በደረታችን መካከል ስላለው የደም ሞተር እየተናገረ አይደለም፡፡ ዐሳብ፣ ስሜትና ውሳኔ ያለበትን ውስጣዊ ማንነት መግለጹ ነው፡፡ ሥጋዊውና ግዙፉ ልብ ከቆመ ደመ ነፍሳዊ ህልውና እንደማይቀጥል$ ዐሳባችን ከተበላሸም መንፈሳዊ ሕይወታችን ወደ ፊት አይራመድም፡፡ ስለዚህ ዐሳብም ልብ መባሉ አቻ ማነጻጸሪያ ነው፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን$ “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” (ምሳ. 4$23) ብሏል፡፡ ውጫዊ አካላችን የውስጣዊ ስሜታችን፣ ዐሳባችንና ውሳኔአችን ሎሌ ነው፡፡ የራሱ የሆነ ውሳኔና ተግባር የለውም፤ አስፈጻሚ አካል ነው፡፡ ምንጩን ሳይደፍኑ ከወራጁ ጋር መታገል ልፋት እንደ ሆነ ሁሉ$ ሐሳብ ካልጸዳም ተግባር ይቀደሳል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለዚህ ለምናስበው፣ ለምንመኘውና ለምንወስነው ነገር ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡

ሰው የምንለው በሥጋና በነፍስ ዐቋም የተገለጸውን እኔ ባይ አካል ነው፡፡ የእውነተኛው ሰው መገለጫ ውጪው ሳይሆን ውስጡ ነው፡፡ ከሚንከባለሉ ዐይኖች ራእይ ያለው ልብ ይመስጣል፡፡ ስለዚህ የሚፈለገው ከአካላዊ ይልቅ መንፈሳዊ ማንነት ያለው ሰው ነው፡፡ ጌታችንም የጠየቀን ንጹሕ ልብን ነው፤ የሰው እውነተኛ ማንነቱ ከውጭ እንቅስቃሴው ይልቅ በልቡ ውስጥ ነውና፡፡ ውጫዊ አካላችን ዜግነቱ ምድራዊ በመሆኑ እዚሁ ይቀራል፡፡ የውስጡ አካላችን ግን ዜግነቱ ሰማያዊ በመሆኑ ወደ ሰማይ ይሄዳል፡፡ የሰው መመዘኛው፣ የግንኙነት ድልድዩ፣ የውሳኔ ሰጪነቱ፣ የፍቅርና የፍርድ ሚዛኑ ያለው በውስጡ ነው፡፡ እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች ይህን የሰው ውስጣዊ ብቃት እንደሚያዩ፤ የእውነት መሠረት የሆነው እግዚአብሔርም ልብን ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ “ልጄ ሆይ$ ልብህን ስጠኝ$ ዐይኖችህም መንገዴን ይውደዱ” ብሏል (ምሳ. 23$26)፡፡ ልቡን የሰጠ የሚያስቀረው ነገር የለም፡፡ ልቡን የሰጠ ጊዜውንና ገንዘቡን ለእግዚአብሔር ለመስጠት አይሰስትም፡፡ ሁሉን የሰጠ እግዚአብሔር ልብን ጠየቀ፡፡ ልብ ያልቀደመበት አገልግሎትና ስጦታ ሁሉ እውነተኛ አይደለም፡፡ ስለዚህ ልብህን ስጠኝ አለ፡፡

እግዚአብሔር ፊትን ሳይሆን ልብን ያያል ተብሎ ተጽፎአል (1ሳሙ. 16$7) ሰው የላይ ዘለግታን ያያል፤ እግዚአብሔር ግን የውስጥ ዐሳብን ይመዝናል፡፡ ሰው ቁመናን አይቶ ይመርጣል፤ እግዚአብሔር ግን ቀላል ልብን ይጥላል፡፡ ሰው በውጫ ቊንጅና ይማረካል፤ እግዚአብሔር ግን በቅን አስተሳስብ ይገኛል፡፡ ሰው ማማርን አይቶ ለራሱ ያጫል፤ እግዚአብሔር ግን ትሑታንን ይዛመዳል፡፡

ነቢዩ ዳዊት ትልቅ ጸሎትን ያቀረበው ስለ ንጹሕ ልብ ነው፤ “አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ ዐድስ” (መዝ. 50/51$10) ብሏል፡፡ ዳዊት የጸለየው የንስሓ ጸሎት ነው፡፡ በመዝሙር 50/51 ላይ የምናገኘው ጸሎት፥ ዳዊት ታማኝ ወታደሩን በማስገደሉ፥ ሚስቱንም ቀምቶ በማመንዘሩ ምክንያት፥ እውነትን አፈላላጊና ፍርድን ሰጪ እግዚአብሔር በነቢዩ በናታን በኩል በገሠጸው ጊዜ የጸለየው የንስሓ ጸሎት ነው፡፡ ይህ መዝሙር ለግለ ሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት የንስሓ ጸሎትና መዝሙር በመሆን እስከ አሁን ያገለግላል፡፡

እውነተኛ ንስሓ ያለፈውን በደል ማመን ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም በቅድስና መኖር ነው፡፡ ስለዚህ ዳዊት ላለፈው ስሕተቱ ይቅርታንለሚመጣው ኑሮው ንጹሕ ልብን ለመነ፡፡ የዳዊትን ሕይወት የበከለው ከልቡ የተጫረው የምኞት እሳት ነው፡፡ የእሳት ትንሽ የለውምና በእንጭጩ ያልተቋጨው ምኞት ለአመንዝራነትና ለነፍሰ ገዳይነት አበቃው፡፡ ክፉ ተግባሩ ከክፉ ምኞቱ መውጣቱን ዐሰበና “አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ” አለ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ለመራመድ የተቀደሰ ዐሳብና የተፈወሰ ምኞት ወሳኝ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዳዊት አስተሳሰቤን ቀይርልኝ፤ በውስጤ አሁንም ክፉ የኀጢአት ዘር እንዳለ ይሰማኛል፤ ከእኔ ለማራቅም ይከብደኛል፤ አንተ ለውጠኝ ማለቱ ነው፡፡ የሕይወት መንገድ የሚነጻው አስተሳሰብ ሲቀደስ ነው፡፡ ጌታም$ “ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው$ እግዚአብሔርን ያዩታልና” አለ (ማቴ. 5፥8)፡፡

እግዚአብሔር ለሕዝቡ ከሰጠው ተስፋ አንዱ የልብ ለውጥ ነው፡፡ በእውነት ይህ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ ሰውን ሁሉ የበደለው ልቡ ነውና፤ በነቢዩ በሕዝቅኤል$ “ጥሩ ውሃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ$ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ፡፡ ዐዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ፤ ዐዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ” (ሕዝ. 36$25-26) ብሏል፡፡

የውሃ የመጀመሪያ ርምጃ ማጽዳት ነው፡፡ ቀጥሎ ማጥራት ነው፡፡ ያ ጥሩ ውሃ ከማንጻት ዐልፎ በውበት የሚያጠራ ነው፡፡ ዮሐንስ በመልእክቱ “የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል”  (1ዮሐ. 1፥7) ያለው ስለዚህ ነው፡፡ የድንጋይ ልብ የተባለው ምክርንና ተግሣጽን የማይቀብል እልከኛ ተፈጥሮ (አስተሳሰብን) ነው፡፡ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ በማለት ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ ሥጋ ሲነኩት በቀላሉ የሚነካ የሚሰረጕድ ነው፡፡ ለእውነት የሚሸነፍ ለፍቅር ስፍራ ያለው ርኅራኄ የሞላበት ልብ እሰጣችኋለሁ ማለቱ ነው፡፡ ንጹሕ ልብን መፍጠር ልብንም መለወጥ ሥልጣኑ የክርስቶስ ነው፡፡ ትልቁ ተስፋም የልባችን ባለቤት መደረጋችን ነው፡፡ ልባችን የእኛ አልሆን እያለ ያምሰናልና፥ የገዛ ልባችንን ምርኮ አድርጎ እንደሚሰጠን ተስፋ ገብቶልናል፡፡ በክርስቶስ ስናምን ከምናገኘው ትርፍ አንዱ የልብ ምርኮ ነውና ደስ ይበልን!

ጌታችን “ልበ ንጽሖች ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና” (ማቴ. 58) በማለት ተናገረ፡፡ እግዚአብሔርን ማየት በሕይወት ላይ ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ነው፡፡ ነገሥታትን በቅርብ ያዩ ሰዎች ማየታቸውን ሲናገሩ ይውላሉ፡፡ በእጃቸው የጨበጡም በጨበጠ እጃቸው ሌላ ላለመጨበጥ እጃቸውን በመሐረብ አስረው የዋሉ ሰዎችን እናውቃለን፡፡ እነዚህ ነገሥታት የኮንትራት ባለሥልጣኖች ናቸው፤ ሽረት ይገጥማቸዋል፡፡ ከዚያ በፊት ሞት መንገዳቸውን ሊያቋርጠው ይችላል፡፡ ዘላለማዊውን ንጉሥ እግዚአብሔርን ማየት ግን ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ነው፡፡

የአብርሃምና የሣራ ገረድ የነበረችው አጋር ጻድቃን የተባሉ አብርሃምና ሣራ ቢከፉባትም እግዚአብሔር ግን ሳይከፋባት በምድረ በዳ እንዳገኛት ተጽፎአል፡፡ አጋር ያናግራት የነበረውን ጌታ “ኤልሮኢ” አለችው (ዘፍ. 16፥13)፤ የሚያየኝን አየሁት ማለት ነው፡፡ በማየት ቀዳሚው እግዚአብሔር ነው፤ ብዙ ዘመን ሲያያት ሲንከባከባት ሲጠብቃት ነበር፡፡ እርሷ ግን አላየችውም ነበር፡፡ አሁን ግን ምንም የሚታይ በሌለበት በምድረ በዳ ውስጥ የበረሓ ጓደኛ የሆናትን እግዚአብሔርን አየችው፡፡ ፍቅሩንና ምሕረቱን ባየች ጊዜ ዳግመኛም ከሁኔታዎች ጋር ዐብሮ እንደማይለወጥ ከቀን ጋራም እንደማይከፋ ባስተዋለች ጊዜ ኤልሮኢ አለችው፡፡ እግዚአብሔር በሚያየን ዘመን በጥፋት ከመሰናከል እንድናለን፡፡ ባየነው ግዜ ግን ደስታና የልብ መተማመን ይሆንልናል፡፡ 

ከአጋር ሌላ እግዚአብሔርን ያየ ያዕቆብ ነው፡፡ ያዕቆብ እንዲህ በማለት ደስታውን ገልጾአል፤ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፤ ሰውነቴም ድና ቀረች” (ዘፍ. 32፥30)፡፡ ድኖ ግርሻት$ እንደ ገና መታመም አለ፡፡ ድኖ መቅረት እግዚአብሔርን የማየት ውጤት ነው፡፡ ያዕቆብ ያመመው ምንድነው? ስንል የአለመርካት ደዌ ነበር፡፡ ተስፋ ያደረገውና ብዙ ዘመን የደከመበት ነገር ርካታን ሊሰጠው አልቻለም፡፡ ይህ የባዶነት ስሜት ከትዳሩ እንዲኰበልል ብቻውንም እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡ እግዚአብሔርንም ባገኘው ጊዜ በጐርፍ መነዳት ውስጥ እንደ ተገኘ ሥር ወይም ዛፍ አለቅህም ብሎ ተጣበቀበት፡፡ እግዚአብሔርም ባረከው፤ ሀብትን ሳይሆን የመርካትን በረከት አደለው፡፡ በዚህ ጊዜ መዳኑ ተሰማውና“እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም ጵንኤል ብሎ ጠራው” (ዘፍ. 3230)፡፡

ነቢዩ ዳዊትም ንጹሕ ልብን ለምኗልና እንዲህ አለ፤ “ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም” በማለት ፈነጠዘ (መዝ. 15/16$8)፡፡ እግዚአብሔር ስውር አይደለም፡፡ ንጹሕ ልብን ስናገኝ በየዕለቱ እናየዋለን፡፡ በተፈጥሮ በሰዎች፣ በፍርድና በምሕረት እግዚአብሔርን በየዕለቱ እናየዋለን፡፡ በውበት የተበጀውን የጥበቡ አሻራ ያረፈበትን ተፈጥሮ ስናይ በደስታ እንሞላለን፡፡ ትልቅ ትምህርትም በተፈጥሮ ውስጥ ተቀምጧልና “እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው” የሚለውን ፊደል ስንቈጥር ሐሤት ይሞላብናል፡፡ ያለ ምንም ምክንያት የሚኖሩትን፣ ታመው የሚድኑትን ስናይ እግዚአብሔርን እናየዋለን፡፡ ባለጠጎች ሲደኸዩ፣ የተዋረዱት ወደ ክብር ሲመጡ እግዚአብሔርን እናየዋለን፡፡

ብፅዕና ጥልቅ ደስታን የምናገኝበት በረከት ነው፡፡ “ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው$ እግዚአብሔርን ያዩታልና” (ማቴ. 58) በማለት ጌታችን አስተምሮናል፡፡ አዎ ደስታን በመፈለግ ደስታ አይመጣም፡፡ ደስታ የሚመጣው በብፅዕና ሕጎች ውስጥ ስናልፍ ነው፡፡ ደስታን አሳዳጆች ደስታን አያገኙትም፡፡ ደስታ የመታዘዝ ውጤት ነው፡፡ እግዚአብሔር በሚያዝንበት ነገር ሁሉ ዐቅም እናጣለን፡፡
የልብ ንጽሕና ምንድነው፤ ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ የልብ ንጽሕና፡-
·        ካለማመን መዳን፣
·        ከክፉ ምኞት መትረፍ፣
·        ከቂም በቀል መፈወስ፣
·        በአዎንታዊ አስተሳሰብ መታነጽ ነው፡፡

የልብ ንጽሕናን እንዴት እናገኛለን፤ ብንል፡-
·        የእግዚአብሔርን ጠባያት በማወቅና በመለማመድ፣
·        ንስሓ በመግባትና ለቅድስና ራሳችንን በማስለመድ፣
·        ይቅር በመባባል፣
የመንፈስ ቅዱስን ኃይል በመማፀን ንጹሕ ልብን ገንዘብ እናደርጋለን እግዚአብሔር ያግዘን!

በጮራ ቍጥር 39 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment