Tuesday, October 6, 2015

የራስ ኩራት

በግር አይቀመስ፣
በአፍ አይዳሰስ፣
በእጅ አይተነፈስ፣
ፊኛ ደም አይረጭም፣
ኩላሊት አይፈጭም
ጥፍርም አያጎርስም፣
አይኬድ በምላስ፣
በጥርስ አይለቀስ፡፡
ልብ አያጨበጭብ፣
አያስብም ቅንድብ፣
ሳንባም አይዋብ፡፡
ዐይንም አይሰማ፣
ጆሮ አይል እማማ፣
ደም አያጠልቅ ጫማ፡፡
የጅ ጣት ቀለበት፣
አይከተት ባንገት፣
ጉትቻ የጆሮ፣
አይሆን ለጉሮሮ፣
ጉርም በየተራ
አይጎርስም እንጀራ፡፡
ሰልካካ አፍንጫ
አይችልም ሩጫ፡፡
ደረት . . . ሱሪ ለብሶ
እግር ከንፈር ነክሶ
ጣፊያን ተንተርሶ
ተረከዝ ተናዶ
ግንባር ከስር ወርዶ
ትከሻ ሲሳለቅ
ወገብ እንባ ሲለቅ
ባት ሲተፋ ምራቅ
ማነው ይህን ያየ፤
እንደዚህ የለየ፤
ይሄ ሁሉ ድንቅ!
ታይቶም አይታወቅ፡፡
ደግሞ ይሄ ብሶ
ጥርስ ምላስ ነክሶ
ፍርድ ቤት ተከሶ
እግር እግርን ገጭቶ
በደንብ ተመታቶ
ሲለያይ ተፋቶ
እጅ ካፍ ተጣልቶ
ሳያጎርሰው ቀርቶ
አላየሁም ከቶ፡፡
ጨጓራ ለአንጀት
ምግብ ሳይልክለት
ለራሱ በልቶበት
ሟጦ ጨርሶበት፡፡
ልብ ደም ሳይሰጠው
ኩላሊት ሲያፋጠው
በቡጢ ሲመታው
መቼ ታየ ለሰው፡፡
ቅንድብ አይን ሲገጭ
ዐይን ሲነጫነጭ
በውሳኔ እንዲላጭ
ሲሳልለት ምላጭ
ማን ያውቃል ሰምቶ፤
በጆሮው አጣርቶ፤
መዳፍም ቀንቶበት
ጣት ሲያጠልቅ ቀለበት
አጡዞት በቡጢ
ብሎትም መናጢ
መዝልጎ ቆንጥጦ
ገዝቶትም ረግጦ
ማነው ይህን ያየ፤
እንደዚህ የለየ፤
ሁሉም አለው ሥራ
ለራሱ ሚያኮራ፡፡
ጆሮም ማዳመጡ
እግርም መሯሯጡ
እጅም መዳሰሱ
ምላስም መቅመሱ
ሳንባም መተንፈሱ
ጨጓራም መፍጨቱ
አፍንጫም ማሽተቱ
አይንም መልከት መልከት
ይሄ ነው ሚያምርበት
የሌላው ይቅርበት
የራሱ ነው ኩራት፡፡
ዐይን ቢል አላይም
አፍንጫ አላሸትም
እጅ አይወጣውም
ስጦታው የለውም
ሁሉም አለው ሥራ
ለራሱ ሚያኮራ
ብርቱና ጠንካራ፡፡

(ከአዲስ መስቀሌ)


በጮራ ቍጥር 39 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment