Sunday, August 5, 2012

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

Read in PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 43 ላይ የቀረበ
ትረካ፥ ከነቅዐ ጥበብ
በገጽ ጥበት ምክንያት በጮራ ቊጥር 42 ላይ የዚህ ዐምድ ጽሑፍ አልቀረበም ነበር። አንባቢ እንደሚያስታውሰው በቊጥር 41 ላይ ወጥቶ የነበረውንና በማኅበረ ቀናዕያንና በደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት የተደረገውን ጉባኤ የተመለከተውን ዘገባ የመጀመሪያ ክፍል፥ በጮራ ቊጥር 41 ላይ አውጥተን ነበር። የዚያን ጽሑፍ ተከታይ እነሆ!

በመርሐ ግብሩ መሠረት ማኅበረ ቀናዕያንን በመወከል ዲያቆን በለው፥ ደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅን ወክሎ ደግሞ ደቀ መዝሙር በቃሉ በየተራና በመደማመጥ ሐሳባቸውን ካስተላለፉ በኋላ፥ በቀረቡት ሁለት ተቃራኒ ሐሳቦች ዙሪያ ታዳሚው አስተያየት እንዲሰጥ የመድረክ መሪው መጋቤ ወንጌል ኅሩይ እምአእላፍ ታዳሚውን ጋበዙ። የመናገር ዕድሉን ለማግኘት በርካታ እጆች ወጡ። ሁሉም ዐጠር ዐጠር አድርገው ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ተደረገ። ሁለቱንም ወገኖች ደግፈውና ተቃውመው አስታያየቶች የሰጡ ነበሩ። ሁለቱን ከመደገፍም ከመቃወምም ርቀው ሚዛናዊ አስተያየት የሰጡም ነበሩ። እኛም ይጠቅማሉ ካልናቸው አስተያየቶች መካከል ጥቂቶቹን ከዚህ ቀጥሎ እናቀርባለን። በመጨረሻም አለቃ ነቅዐ ጥበብ የሰጡትን ሐሳብ በማካተት ዘገባችንን እናጠቃልላለን።


ለሌላው ትምህርት ይሰጣል ብለን የመረጥነው አንዱ አስተያየት ሀብተየስ የተባለ ሰው የሰጠው ነው። የጀመረው ራሱን በማስተዋወቅ ነበር።

“ሀብተየሰ እባላለሁ የመጣሁት ከማኅበረ ቀናዕያን ነው። ከእኛም ከደቂቀ እስጢፋኖስም ወገን በሁለት ዙር የቀረቡትን ሐሳቦች አዳምጫለሁ። እዚህ ያለው ታዳሚ ማኅበረ ቀናዕያን ለእናት ቤተ ክርስቲያን የሚያስቡና የሚቈረቈሩ አባላትን ያቀፈ ማኅበር መሆኑን እንዲረዳ እፈልጋለሁ። ፍጹም የሆነ ግለ ሰብም ሆነ ቡድን የለም። አይኖርምም። ሁሉም የየራሱ ድካምና ብርታት አለው። ከዚህ እውነታ አንጻር ማኅበራችን የራሱ ብርቱ ጎኖች፥ ደካማ ጎኖችም አሉት። በዲያቆን በለው በኩል ከተገለጸው ሐሳብ ውስጥ በበርካታ ጉዳዮች ብስማማም አንድ መስተካከል ያለበትና በማኅበራችን ውስጥ ሥር የሰደደ፥ ነገር ግን በቶሎ መነቀል ያለበት ክፉ አመለካከት እንዳለ መገንዘብ ችያለሁ። እርሱም እመቤታችንንና ቅዱሳንን የወደድን እየመሰለን፥ ሳናውቀው ጌታችንን፣ አምላካችንንና መድኀኒታችንን ኢየሱስን እየተቃወምን የመገኘታችን ጒዳይ ነው።

“ለምሳሌ፥ ዲያቆን በለው የደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትን የተቃወመበት አንዱ ነጥብ ‘በስብከታቸው ላይ የእመቤታችንንና የቅዱሳንን ስም አያወሱም፤ ሁል ጊዜ ኢየሱስ፥ ኢየሱስ ብቻ ነው የሚሉት’ የሚል ነው። እንዲህ ሲል በእውነቱ እጅግ ነው የከበደኝ። የእመቤታችንንና የቅዱሳንን ስም እንደየስብከታችን ይዘት ማውሳት እንዳለብን የታወቀ ነው። የምናወሳቸው ግን የጌታችንን አዳኝነት ለማጒላትና የእርሱን ተኣምራት ለመንገር መሆን አለበት እንጂ፥ እርሱን ተክተው እንዲሰበኩ መሆን የለበትም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን፥ ምን ጊዜም ልንሰብክ የሚገባን የተሰቀለውን ክርስቶስን መሆን አለበት። በኮሌጅ ቈይታዬ ከስብከት ዘዴ ኮርስ የተማርሁትም ይህንኑ ነው። ስለዚህ የማኅበራችን አባላትና አመራሮች ሁሉ ኢየሱስ በመሰበኩ ደስ ሊለን እንጂ ልንበሳጭ አይገባንም ባይ ነኝ።” ሲል ሞቅ ያለ ጭብጨባ ንግግሩን አጀበው። “እኔ እንዲህ ያልሁት አንዱን ወገን አስደስቼ አንዱን ለማስከፋት ሳይሆን፥ እውነትን መመስከር ስላለብኝ ነው። ርግጥ ይህ አስተያየቴ ዋጋ ሊያስከፍለኝ እንደሚችል ዐውቃለሁ። ቢሆንም ለመኖር ብዬ ይህን እውነት ከዚህ በኋላ ልሸሽግ አልችልም። እየዋሹ መኖር ሰልችቶኛል። ስለ እውነት ተናግሬና እውነትን መስክሬ የሚመጣውን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።” አለና አስተያየቱን ቋጨ።

ሌላው የተመረጠው አስተያየት የትርሲተ ወልድ አስተያየት ነው። ትርሲተ ወልድ የመጣችው ከደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ነው። አስተያየቷ ይህ ነበር። “እኔ በሁለቱ ወገኖች መካከል እየተካረረ የመጣውንና ለዚህ ጉባኤ መዘጋጀት ምክንያት የሆነውን ጒዳይ ከመነሻው አንሥቶ ለመከታተል ሞክሬያለሁ። ነገሩን ስመለከተው በአይሁድና በክርስቶስ፥ በአይሁድና በሐዋርያት መካከል የነበረውን ውዝግብ ነው የሚያስታውሰኝ። አይሁድ ክርስቶስንም ሆነ ሐዋርያትን ሲቃወሟቸው የነበረው ለእግዚአብሔር ቀንተው እንጂ እግዚአብሔርን ለማሳዘን ፈልገው አይደለም። ነገር ግን ሥራቸው ሲመዘን እግዚአብሔርን መቃወምና ማሳዘን ሆኖ ተገኘ። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አልቻሉም። ዛሬም እንዲህ ዐይነት ተግባር እየፈጸምን ያለን ካለን፥ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝብንምና ልንመለስ ይገባል። ስለ ኢየሱስ ስም መከራ እየተቀበልን ያለን ወገኖችም ደስ ሊለን፥ የመከራው ተካፋዮች በመሆናችን ሐሤት ልናደርግ፥ ስለሚያሳድዱንም ልንጸልይላቸው ይገባናል እንጂ እነርሱን መጥላትና በእነርሱ ላይ ክፉ መመኘት የለብንም። ጌታ ለሰቀሉት አይሁድ፥ ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስም በድንጋይ ይወግሩት ለነበሩት ምሕረትን እንደ ለመኑላቸው እኛም አሳዳጆቻችን ለእግዚአብሔር የቀኑ በመምሰል፥ ነገር ግን ባለማወቅ እያደረጉት ላለው ኢክርስቲያናዊ ክፉ ሥራቸው መማለድ ነው የሚገባን። ከዚህ ውጪ የምናስብና የምናደርግ ከሆነ ግን ስለ ስሙ የምንቀበለውን ለክብር የሆነውን መከራ ዋጋ ቢስ እናደርገዋለን። የእኔ አስተያየት ይህ ነው፤ አመሰግናለሁ” አለች። ታዳሚውም አጨበጨበ።

ሦስተኛው አስተያየት ከዚያው ከደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ በመጡት መሪጌታ ላእከ ኢየሱስ የተሰጠ ነው። መሪጌታ ላእከ ከሁሉ በፊት አንዱ ሌላውን ጠርቶ ሳያነጋግረውና ስለሚያምነው እምነቱ ሳይጠይቀው፥ “ተሐድሶ” እንዲሁም “መናፍቅ” እያለ ስም እየሰጠ ከሚያሳድድበት ዘመን እየተላቀቅን መሆኑን ማየት ስለ ቻልሁ አምላኬን፥ ሁሉ በተከናወነበት በክርስቶስ ኢየሱስ ስም አመሰግናለሁ። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ማንም እየተነሣ “እገሌ መናፍቅ ሆኗልና መወገዝ አለበት” የሚል ክስ ይዞ ከቀረበ፥ ክሱ የቀረበበት ሰው ተጠርቶ በአግባቡ ሳይጠየቅ ተወግዘሃል ይባላል። ለጥያቄማ ማን አቅርቦት! ከሳሾቹ ይህን መች ይፈልጋሉ? ይህ እድል ሳይሰጠው እነርሱ በወጠኑት መንገድ ከቤተ ክርስቲያን እንዲባረር ነው የሚፈልጉት። ስለዚህ በአግዓዝያን አብያተ ክርስቲያናት አማካይነት በዚህ አይሁዳዊ አካሄድ ውስጥ ላሉት ትምህርት ለመስጠት ይህ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱ አጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው።

“በደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና በማኅበረ ቀናዕያን መካከል ስለ ተፈጠረው ውዝግብ ሁለቱም ወገኖች በተወካዮቻቸው በኩል ያቀረቡትን ሐሳብ በንቃት ተከታትያለሁ። እኔ ከዚህ ቀደም ብሎም በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን ችግር መነሻ በማድረግ፥ አንዱ ሌላውን ሲወነጅልና ራሱን ሲከላከል እንደ ነበረ አስታውሳለሁ። በሁለቱም በኩል ‘እኔ ልክ ነኝ፤ እርሱ ተሳስቷል’ የሚል አቋም ተይዞ ነበር። ልክ ነኝ ባዩ እውነተኛ ነኝ ለማለት የሚያቀርበው የራሱ ማስረጃ ይኖረዋል። መከራከሪያዎቹን በመጽሐፍ ቅዱስ ስመዝናቸው ግን የማኅበረ ቀናዕያን ልክ ነኝ ባይነት መጽሐፍ ቅዱስንና በዚያ ላይ ተመሥርተው የጥንት አባቶች ያስተላለፉትን እውነተኛ ትምህርት ያልተከተለ ሆኖ አገኘዋለሁ። ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ይዛ የመጣችውን ማንኛውንም ነገር፥ ማለትም፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለውንና ከእርሱ ጋር የሚቃረነውን ትምህርት፥ ሥርዐት፥ ባህል፥ ልማድና ወግ ሁሉ የእውነተኛው የክርስትና ሃይማኖት መለኪያ አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያ ይታያል። የደቂቀ አስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ደግሞ፥ ይህን የማኅበረ ቀናዕያን ሐሳብ ነው የሚቃወሙት። በእኔ እምነት ከመጽሐፍ ቅዱስና በዚያ ላይ ከተመሠረተው የአበው ትምህርትና ሥርዐት ውጪ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚያስገቡን አይደሉምና ዋና የሃይማኖት ጒዳዮች ተደርገው ሊያጣሉን አይገባም። በሌላ በኩል ግን የታሪካችን፥ የባህላችን፥ የልማዳችንና የወጋችን አካላት በመሆናቸው በየራሳቸው ሊታዩ ይገባል።               

“እንዲህ ካልሆነ ሰማያዊውን ወንጌል ከምድራዊው የሰው ልማድና ወግ፥ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ከሰው ሐሳብ፥ ሕይወት የሚገኝበትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት፥ ሕይወት ከማይገኝበት ምድራዊ ፍልስፍና መለየት እንቸገራለን። በክርስትና ስም ተሰብስበን የምናራምደው ሌላ ምድራዊ አጀንዳ ከሆነ ከዘላለም ሕይወት አጀንዳ ወጥተናል። ስለዚህ ቆም ብለን ማሰብ አለብን። ታሪካችን፥ ባህላችን፥ ሥርዐታችን፥ ልማዳችንና ወጋችን ለእኛ ትልቅ ዋጋ ያላቸው ቢሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን የሕይወት መንገድ አይተኩም። እዚሁ እኛ ዘንድ ብቻ ቀሪ ናቸው። እነዚህን ሁለት ነገሮች በየፊናቸው መመልከት እንጂ መደባለቅ ወይም አንዱን በሌላው መተካት አይቻልም። በሃይማኖት ስም የተሰባሰበ ማንኛውም አካል በዋናነት ሊያስብ የሚገባው የዘላለም ሕይወት ስለሚያገኝበት ነገር ነው እንጂ ስለ ሌላ መሆን የለበትም። በሃይማኖት ጥላ ሥር ሆኖ ስለ ሌሎች ጒዳዮች እያሰበና እየተጋደለ ከዘላለም ሕይወት ውጪ ቢሆን ምን ይጠቅመዋል? ስለዚህ ማንኛችንም በመጽሐፍ ቅዱስ ለተገለጠው የእግዚአብሔር እውነት ቅድሚያ መስጠት አለብን።” አሉና አስተያየታቸውን ደመደሙ።      

በመጨረሻም አለቃ ነቅዐ ጥበብ የማጠቃለያ ሐሳብና አባታዊ መልእክታቸውን ለማስተላለፍ ወደ መድረኩ ወጡ። አለቃ የሚናገሩትን ለመስማት የታዳሚዎቹ ጆሮዎች ይበልጥ ተከፈቱ። ነገር በዐይን ይገባል እንደሚባለውም ዐይኖች ሁሉ በእርሳቸው ላይ ተተከሉ። አለቃ ለጉባኤው ታዳሚዎች ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ፥ ንግግራቸውን ቀጠሉ። “ዘመኑ ምን ቢሠለጥን፥ ማንኛውም ሰው አምኖበትም ይሁን ወርሶት፥ የወደደውን ሃይማኖትን የመከተልና የማምለክ መብት በሕገ መንግሥት የተረጋገጠ ቢሆንም፥ ወንጌል ዛሬም በተቃውሞ ውስጥ እየተሰበከ መሆኑ ብዙ ሊያስገርመን አይገባም። ይህ የወንጌል ጠባይ ነው። የወንጌል ቀንደኛ ተቃዋሚ ጠላት ዲያብሎስ፥ በወንጌል መሰበክ ምክንያት ብዙዎች ከእርሱ ግዛት ስለሚፈልሱና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ስለሚገቡ በዚህ ደስ አይሰኝም። ስለዚህ በተሰበከላቸው ወንጌል ያመኑትንና መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ በሞቱ የኀጢአታቸውን ዕዳ የከፈለላቸው መሆኑን የተቀበሉትን ሰዎች፥ ካመኑትና ከተቀበሉት ከዚህ ሕይወት እንዲወጡና ወደ ኋላ እንዲመለሱ ለማድረግ በብዙ ይጥራል። ለዚህም መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀመው በወንጌል ያላመኑትንና የእርሱን ፈቃድ የሚፈጽሙትን ሰዎች ነው። ወንጌልና ተቃውሞ ዐብሮ ኗሪ ናቸውና መደነቅም መደንገጥም አያስፈልግም።

“ሌላውን ሁሉ በየሚዲያው ስትነጋገሩበት ስለ ቈያችሁና ጊዜውም እየሄደ ስለ ሆነ፥ እኔ ማተኰር የምፈልገው ከሁለቱ ወገኖች ውዝግብ ጀርባ ባለው እውነት ላይ ነው። የሚጠቅመንም እርሱን ማስተዋል ነው።” አሉና ለመናገር የፈለጉበትን ርእሰ ጒዳይ አስጨበጡ።   

“እዚህ የቆምሁት ወንጌል የሚያስከፍለውን ዋጋ ለማስታወስ ነው እንጂ፥ በወንጌል ምክንያት የሚነሣውን ተቃውሞ መቀነስ ስለሚቻልበት ሁኔታ አቅጣጫ ለማሳየት አይደለም። በወንጌል ምክንያት የሚነሣውን ተቃውሞ መቀነስ ካስፈለገ መደረግ ያለበት ስለ ተሰቀለው ክርስቶስ አዳኝነት አለመናገር ነው። ስለ ተሰቀለው ክርስቶስ ሳይሆን፥ ሰዎች በምድራዊ በረከት ስለሚባረኩበት፥ ስለ ስኬት፥ ስለ ፈውስ፥ ሌሎችን ሃይማኖቶች በመቃወም ብንሰብክ በዐጭር ጊዜ ብዙ ተከታይ እናፈራለን። እዚህ ላይ የተዘረዘሩት ብዙዎቹ ነገሮች አስፈላጊዎቻችን በመሆናቸው በአግባቡ መሰበክ የለባቸውም እያልሁ አይደለም። ዋናውና ትልቁ ጒዳይ የተሰቀለው መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ መሰበኩ ነው ለማለት ነው። ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገቡት ስለ ተሰቀለው አዳኝ ሲሰበክላቸውና በእርሱ ሲያምኑ ነው። ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፥ ‘እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን’ ያለው።

“መቼም የተሰቀለውን ክርስቶስን ስንሰብክ፥ የእርሱን ስፍራ የቀሙ ብዙ ነገሮች መኖራቸው አይካድምና ‘እነ እገሌንስ፥ እነ እገሊትንስ ምን ልናደርጋቸው ነው?’ የሚል ተቃውሞ መነሣቱ አይቀርም። በዚህ ጊዜም ቢሆን ለድርድር የማይቀርበውን የእርሱን አዳኝነት ብቻ መናገራችን አይቀርምና ተቃውሞው ሊያይል ይችላል። ቅድም ዲያቆን በለው ሲናገር በደቂቀ እስጢፋኖስ ተማሪዎች ላይ ያቀረበው አንዱ ክስ ‘ሁል ጊዜ የሚሰብኩት ስለ ኢየሱስ ነው፤ ስለ ሌሎቹ አይሰብኩም’ የሚል ነበር። አንዱ አስተያየት ሰጪም ተችቶታል። በእውነቱ፥ ይህ ምን ይባላል? በአንድ በኩል የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ አለመረዳት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያን ነኝ የሚለውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውጪ በሆኑ ሌሎች ትምህርቶች የሚመራውን ወገን ባልሆነ መንገድ ለመቀስቀስ የሚደረግ ጥረት ነው። ከሁለተኛው ይልቅ የሚከፋው ግን የመጀመሪያው ነው፤ - የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ አለመረዳት። እውን በወንጌል ሊሰበክ የሚገባው ማን ነው? ክርስቶስ ብቻ አይደለምን?” ሲሉ አለቃ፥ ታዳሚው ምላሹን በሞቀ ጭብጨባ ሰጠ።

“አዎን! ሊሰበክ የሚገባው የተሰቀለው ክርስቶስ ብቻ ነው። ሰዎች ሁሉ አምነው ይድኑ ዘንድ ከእርሱ በቀር የሚሰበክ የለም። ወንጌል ስለ ተሰቀለው ክርስቶስ አዳኝነት የሚናገር የእርሱ መልካም ዜና ነው እንጂ ሌላ ማንም ፍጡር አይሰበክበትም። ታዲያ በቤተ ክርስቲያን የተሰቀለውን ክርስቶስን ብቻ መስበክ እንዴት ወንጀል ሊሆን ይችላል? በዚህ ጒዳይ ላይ ክስ ያቀረቡት ማኅበረ ቀናዕያን ክርስቲያኖች ናቸው ወይስ ሌሎች?

“ቀድሞ ጌታ ኢየሱስን ይጠሉ የነበሩትና በእርሱ ስም ለምን ይሰበካል? ስሙስ ለምን ይጠራል በሚል ይበሳጩ የነበሩት አይሁድ፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ናቸው። የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በእነዚህ የወንጌል ተቃዋሚዎች እና በሐዋርያት መካከል ልዩነትን ፈጥሮ የነበረው የኢየሱስ ስም፥ ዛሬም ድረስ በሰዎች መካከል ልዩነትን መፍጠሩና እያነጋገረ መቀጠሉ አስደናቂ ነገር ነው። ወንጌል በተቃውሞ ውስጥ ቢሰበክም ተቃውሞ ሊያቆመው እንደማይችል ግን ከቅዱስ መጽሐፍ አንበበናል። ከታሪክም ተገንዝበናል። ዛሬም ይህንኑ በዐይናችን እያየን ነው።

“እስኪ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከተመዘገበው የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ ጥቂት እንመልከት።” አሉ። የነገሩን መነሻ በቃላቸው እያብራሩ፥ የሚፈልጉትን ኀይለ ቃል የያዘውን ጥቅስ በየመካከሉ ማንበብና ማስረዳት ቀጠሉ። “ሁላችሁም እንደምታስታውሱትና በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 3 እና 4 ላይ የተጻፈው ታሪክ እንደሚያስረዳው፥ ሐዋርያት ጴጥሮስና ዮሐንስ ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይወጡ ነበር። አንድ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ዐንካሳ የነበረና ወደ መቅደስ ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን የነበረ ሰው አግኝተውም፥ ጴጥሮስ “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ” ብሎ እጁን ይዞ ሲያነሣው፥ ሰውዮው ደኅና ሆኖ ቆሟል። ወዲህና ወዲያም በመመላለስ መፈወሱን አረጋገጠ። ልመናውን ትቶም እግዚአብሔርን እያመሰገነ ከሐዋርያት ጋር ወደ መቅደስ ገባ። ይህ ተኣምር በብዙዎች ዘንድ መገረምን ፈጥሮ የብዙዎችን ትኲረት ሳበ። የተደረገውን ይህን ድንቅ አይተውና የሐዋርያትን ምስክርነት ተቀብለው ዐምስት ሺህ የሚያህሉ ሰዎች አመኑ። ይህን ተከትሎም የካህናት አለቆች፥ የመቅደስ አዛዥ ሰዱቃውያን፥ ሐዋርያት “ሕዝቡን ስለ አስተማሩና በኢየሱስ የሙታንን ትንሣኤ ስለ ሰበኩ ተቸግረው፥” ወደ ወኅኒ አወረዷቸው። ይህን ኀይል ያደረገውን የጌታችንን የስሙን ሥልጣን ማሰርም ሆነ ማገድ አይችሉምና ስሙን የተሸከሙትን ሐዋርያትን አሰሯቸው። እንዲህ በማድረጋቸው እንቅስቃሴውን የሚገቱ መስሏቸው ይሆናል። ይህ ግን የሚቻል አይደለም።

“በማግሥቱም በሸንጎ ፊት አቁመው ‘በምን ኀይል ወይስ በማን ስም እናንተ ይህን አደረጋችሁ?’ ሲሉ መረመሯቸው። ሐዋርያትም ‘እኛ ዛሬ ለድውዩ ሰው ስለ ተደረገው መልካም ሥራ ይህ በምን እንደ ዳነ ብንመረመር፥ እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፥ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማእዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው። መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” የሚል መልስ ሰጡ። እነርሱ ግን በምስክርነታቸው ደስ አልተሰኙም። ‘የተፈወሰውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ሲያዩ የሚመልሱትን ዐጡ። ከሸንጎም ወደ ውጭ ይወጡ ዘንድ አዝዘው፥ በእነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ? የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፥ እንሸሽገው ዘንድ አንችልም፤ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው ብለው እርስ በርሳቸው ተማከሩ። ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው። እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው’ (ሐ.ሥ. 4፥15-20)።

“ልብ በሉ!” አሉ አለቃ መጽሐፉን አትሮንሱ ላይ አስቀምጠው፥ የመጨረሻውን ጥቅስ ለማብራራት ወደ ፊት ጠጋ እያሉ። “ልብ በሉ! እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች በሐዋርያት እጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተደረገውን ተኣምር ሊያስተባብሉ እንደማይችሉ ተረድተዋል። ለዚህም ነው ‘የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፥ እንሸሽገው ዘንድ አንችልም፤’ ያሉት። ለእውነት ከመሸነፍና ከመገዛት ይልቅ እውነትን በሥልጣናቸውና በማያዋጣ መንገድ ለማፈን ነበር የሞከሩት። አንዱ ስልታቸውም ነገሩ ከዚህ በላይ እንዳይስፋፋ ማድረግ ነበር። ለዚህም መወሰድ ያለበትን ርምጃ ሲያስቀምጡ፥ ሐዋርያትን “ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው” አሉ። ወገኖቼ ሆይ! እነዚህ ሹማምት አላፈሩም፤ ይህንኑ ውሳኔአቸውን ለሐዋርያት አሳወቋቸው። ‘በኢየሱስ ስም ፈጽማችሁ እንዳትናገሩ! እንዳታስተምሩ!’ ሲሉ አዘዟቸው። ይህ ዐዋጅ ቢታወጅበትም፥ ሐዋርያት ግን “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር” (ሐ.ሥ. 5፥42)። እንዲህ የመናገር መብት እንኳ በሌለበት በዚያ ዘመን ወንጌል በአስገራሚ ፍጥነት እንደ ሰደድ እሳት ለብዙዎች የተዳረሰ መልካም ዜና ሆኗል። ብዙዎችን ወርሷል። እንዲያውም ዕልፍ ብሎ ምዕራፍ 6 ቊጥር 7 ላይ “የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፥ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።” በማለት ዐዋጁ ከወጣበት ቤት ብዙዎችን መማረክ መቻሉን ወንጌላዊው ሉቃስ መስክሯል። ዛሬም እንደዚያው ነው” ሲሉ አዳራሹ በጭብጨባና በእልልታ ተናጋ።

“ሐዋርያት ለዚህ የሰጡት ምላሽ ምን ይመስላችኋል?” አሉና መልስ የማይሻ ጥያቄ አቀረቡ። ቀጠሉና፥ “የሐዋርያት ምላሽ እኒያ የሃይማኖት መሪዎች እንደ ፈለጉት ሆኖ አልተገኘም። ዛቻና ማስፈራሪያቸውም አልሠራም። ‘እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ’ በማለት፥ ለመልስ አስቸጋሪ የሆነ ጥያቄ አቀረቡላቸው። በዚህ አስቸጋሪ ጥያቄ አእምሮአቸው ተወጥሮ ሳለም፥ ‘እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም’ አሉአቸውና አቋማቸውን ግልጽ አደረጉላቸው። እነርሱም የነበራቸው አማራጭ እነርሱን ከእስር መፍታት ነበረና ፈቱአቸው።

“ሲቃወሙትና ሲያሳድዱት እየሰፋ የሚሄደው ወንጌልና በእርሱ የሚሰበከውና የሚፈውሰው የኢየሱስ ስም፥ ከዚህ እስር፥ ዛቻና ማስፈራሪያ በኋላ ብዙም ሳይቈይ፥ ሌላ ነውጥ አስነሥቶ ሐዋርያትን ዳግም ለእስር እንደዳረገ በቀጣዩ ምዕራፍ ውስጥ እናነባለን (ምዕራፍ 5)። በሐዋርያት እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ መደረጉን ተከትሎ፥ እነዚያው የሃይማኖት መሪዎች በቅንአት ተነሡባቸውና ሐዋርያትን ወደ ወኅኒ አወረዷቸው። የጌታ መልአክ ግን ከወኅኒ አውጥቶ፥ “ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ አላቸው።” እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ። ወደ ወኅኒ የጨመሯቸው የካህናት አለቆች፣ የሽንጎ አባላትና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ከወኅኒ ሊያስመጧቸው ቢልኩ ግን ሐዋርያት አልተገኙም፤ የተገኙት በመቅደስ ሲያስተምሩ ነበር። ወኅኒው በአግባቡ የተቈለፈ፥ ዘቦቹም በስፍራቸው ነቅተው የሚጠብቁ ቢሆንም፥ ሐዋርያት የወጡበት መንገድ ተኣምራዊ ነበርና ተደንቀዋል። በፊታቸው ካቀረቧቸው በኋላ ግን ሊቀ ካህናቱ እንዲህ አላቸው። “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው።” ሐዋርያት ግን ሌላ ጥያቄ የማያስከትል ምላሽ ሰጡ። “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” አሉ። አክለውም፥ “እናንተ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤ ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሓን የኀጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ፥ ራስም መድኀኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው። እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቈጡ ሊገድሉአቸውም ዐሰቡ።”

በዚህ ሁሉ ውስጥ ሐዋርያት ትክክለኞች ቢሆኑም፥ የሃይማኖት መሪዎቹ በእልከኛነት በመጽናት፥ በገማልያል ምክር ረገብ ብለው፥ ሐዋርያትን በማመስገን ፈንታ ገርፈውና በኢየሱስ ስም ዳግመኛ እንዳያስተምሩ አዝዘው ፈቱአቸው። ዛሬም ይኸው ነው። ኀላፊነት የማይሰማቸውና አደራቸውን በሚገባ ያልተወጡ የሃይማኖት መሪዎች፥ ተደላድለው የተቀመጡበትን ወግና ልማድ በእግዚአብሔር ቃል ከመፈተሽና ወደ እውነት ከመጠጋት ይልቅ፥ እውነትን ሲቃወሙና ሲያወግዙ ይታያል። ያው አይሁዳዊ፥ ፈሪሳዊና ሰዱቃዊ ልማድ ነው።         

አለቃ ጥቂት ዐሰብ አደረጉና፥ “እኔ ግርም የሚለኝ” አሉ፥ “እኔ ግርም የሚለኝ፥ የእነዚህ ሰዎች ችግር ምን ነበር? ርግጥ ‘ኢየሱስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ብላችሁ ለምን በስሙ የሙታንን መነሣት ትሰብካላችሁ?’ የሚለው ዋናው ችግራቸው ነበር። ለዚህ ነው ትንሣኤ ሙታንን የሚቃወሙት ሰዱቃውያንም ከካህናት አለቆች ጋር በሸንጎው ዋና ተቃዋሚ ሆነው የታደሙት። እነርሱ በሐሰት ‘አልተነሣም’ ያሉት ኢየሱስ ሕያው መሆኑን በስሙ በሚሠራው ድንቅ ሥራ እያረጋገጠ፥ እነርሱ ግን ‘ካፈርሁ አይመልሰኝ’ ብለው በሐሳባቸው መጽናታቸው ይገርማል። እነዚያስ በዚህ ምክንያት ኢየሱስንና በስሙ የሚደረገውን ድንቅ ጠሉ። ስሙንም ከቤተ መቅደስና ከምኲራብ አሳደዱት።  ቤተ መቅደስና ምኲራብ ያሳደዱትን ይህን ታላቅ ስም በመጀመሪያ የተቀበለችው ቤተ ክርስቲያን፥ አክብራ መያዝ ሲገባት ለጒዳዩ ሌላ ስያሜ እየሰጠች ስሙን ስትገፋና ስታሳድደው ኖራለች። ይሁን እንጂ ስሙ እያሸነፈና ብዙዎችን እየማረከ መምጣቱ አልቀረም። እንደ ትናንት፥ ዛሬ ስሙን መጥራት አይከለከልም፤ ነገር ግን በዚህ ስም የሚያስተምር እውነተኛ አገልጋይ ‘በስሙ ለምን ታስተምራለህ? ስሙንስ ለምን ትጠራለህ?’ ባይባልም፥ በሌላ ርእስ ይከሰስና “መናፍቅ ተሐድሶ” ሆኗል ይባላል። የክሱ ርእስ መለወጡ እንጂ ነገሩን አገላብጠን ብናየው ዞሮ ዞሮ ‘ኢየሱስ ለምን ይሰበካል?’ ነው ጉዳዩ።

“ዲያቆን በለው የነገሩን አካሄድ ስላላወቀበት ፍርጥ አደረገና ‘የሚሰብኩት ስለ ኢየሱስ ብቻ ነው’ ሲል የደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎችን ከሰሳቸው እንጂ፥ ይህ እኮ የክርስቶስን ወንጌል የሚሰብኩትን ሁሉ ‘መናፍቅ’ እያሉ ስም የሚያወጡ እንደ ማኅበረ ቀናዕያን ያሉ ክፍሎች ሁሉ ውስጥ ውስጡን የሚያሰሙት ተቃውሞ ነው። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስን መቃወማቸውን ሌላ ልብስ ሊያለብሱትና ሊያሳስቱን አይገባም። ዛሬም በግልጽም በስውርም ኢየሱስንና በስሙ የሚሰበከውን ወንጌል የሚቃወሙትንና በአይሁድ መንገድ እየሄዱ ያሉትን የምንመክራቸው በገማልያል ምክር ነው። “ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ ዐሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።” (ሐ.ሥ. 5፥38-39)። ታዳሚው አጨበጨበ። አለቃም ወደ ወንበራቸው ሲመለሱ፥ በአዳራሹ የተቀመጠው ሁሉ ተነሥቶ ተቀበላቸው።

2 comments:

  1. አለቃ ነቅዐ ጥበብ may God bless you !! God bless Ethiopia and its people,in the name of the most high GOD ;Jesus Christ amen!!

    ReplyDelete
  2. thank you Aleka, When I sea people like you , I remind my self that our church will be back on track one day

    ReplyDelete