Monday, July 30, 2012

የጋብቻ አባወራነት

Read in PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
መግቢያ፡-
የጋብቻ ቅንጅት” በተባለው በአንደኛ ጽሑፋችን በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተገለጠው የጋብቻ ቅንጅት እግዚአብሔር በሁለት ባልና ሚስት መካከል የሚገኝበት ቅንጅት ነው፡፡ በቅንጅቱም ባልና ሚስት ፊት ለፊት ተያይተው የልብ መግባባት እንደሚኖራቸው ተመልክተናል፡፡ በአንድ በኩል የባልና ሚስት እኩልነት እግዚአብሔር እነርሱን በመፍጠሩና በመውደዱ ለክብሩ እንዲኖሩ በዓለም በማስቀመጡ ተገልጾአል፡፡ በሌላ በኩል ግን በጋብቻ ውስጥ የሁለቱንም ኀላፊነት ስንመለከት ጐላ ያለ ልዩነት ይታያል፡፡ በመካከላቸው ያለው የፍቅር ግንኙት እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ እንዲሠራ ባልና ሚስት በፈጣሪያቸው ከመጀመሪያ በጋብቻ ውስጥ የተፈጠረውን መሠረታዊ ልዩነት እንዲያስተውሉ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ በጋብቻ ውስጥ ያለው አባወራነት ይህን ልዩነት እንዴት እንደሚያብራራ አሁን ልንመለከት እንችላለን፡፡

የአባወራነት ሕግ
የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ ይህ የሐዋርያው ጳውሎስ ቃል ሊያስደነግጠን ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ቃል የሚያመለክተን አባወራነት የተጀመረው በዔድን ገነት ውስጥ ሳይሆን ከዘላለም በሥላሴ ዘንድ ነው፡፡ እኛም ስለ ሥላሴ ስንናገር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንላለን እንጂ ወልድ አብ መንፈስ ቅዱስ አንልም፡፡ በመለኮታዊ ባሕርይ አንድና እኩል ሲሆኑ በተግባራቸው የሚገለጥና በአባወራነት የተመሠረተ ቅደም ተከተል አላቸው፡፡ በምድራዊ አባትና ልጅ መካከል ያለውን ያንጸባርቃል፡፡  


ማንኛውም ድርጅት ሕጎችና ደንቦች የሚያወጣለትና ኀላፊነትን የሚወስድ አባወራነት ያስፈልገዋል፡፡ የመሪነት ኀላፊ ከሌለ ግን ከፍተኛ መደናገርን ከመፍጠሩም በላይ ሥራውን ከንቱና ፍሬ ቢስ ያደርገዋል፡፡ እንግዲህ በኅብረተ ሰብ መካከል ከሁሉ አነስተኛ የሆነና በእግዚአብሔር የተቀደሰ ቤተ ሰብ አባወራነት ሲኖረው አስገራሚ አይደለም፡፡

በዚህ ረገድ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ በተፈጠሩት በአዳምኛ በሔዋን ቅንጅቱ እንዴት ሊታይ ይችላል? አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና በኋላም ሔዋን ተፈጠረች ሲል ሐዋርያው ጳውሎስ ያሳስበናል፡፡ በሥነ ፍጥረት ውስጥ ቀጥተኛ የሆነ የአፈጣጠር ተራ አለ፡፡ አዳምም ከሔዋን የተፈጠረ ሳይሆን ሔዋን ከአዳም የተፈጠረችና ለእርሱም ረዳትና ጓደኛ እንድትሆን እግዚአብሔር አዳምን ወደ ሔዋን ያመጣ ሳይሆን ሔዋንን ወደ አዳም እንዳመጣ እንገነዘባለን፡፡ ይህንም ቀደምትነት አዳም ለእንስሳቱ በሙሉ ስምን በማውጣት ለሔዋንም ስምዋን በመስጠት ገልጦ አሳይቶአል፡፡ በእርሷ ላይ ያለውን አባወራነት ያመለክታል፡፡ በዚህም ሁኔታ ፍጹም ደስታና አንድነት በመካከላቸው ይታይ ነበር፡፡ እንዲሁም ከመጀመሪያ ጀምሮ በባልና ሚስት መካከል ያለው ግንኙነት በአብና በወልድ መካከል ያለውን ውብና ምስጢራዊ ግንኙነት እንዲያመለክት በሐዋርያው ጳውሎስ በሚቀጥለው ቃል ተገልጦልናል፡፡ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ የሴትም ራስ ወንድ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ በተጨማሪም ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ በባልና ሚስት መካከል ያለው ግንኙነት በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል እንዳለው የተቀደሰ ዐይነት ግንኙነት መሆኑን ይገልጻል፡፡

አባወራነት በባል በኩል ሲታይ

በምሳሌና በትእዛዝ መጽሐፍ ቅዱስ ደረጃ በደረጃ የአባወራነት ሕግ ለባል ምን እንደሚል ይገልጽልናል፡፡ እርሱም ለቤተ ሰቡ ጀማሪና አቅኚ በመሆኑ ውሳኔዎቹን ለማውጣት ኀላፊነትና ውሳኔዎቹን ለመፈጸም  እግዚአብሔር የሰጠው መንፈሳዊ ሥልጣን እንዳለው እንረዳለን፡፡ ከውድቀትም በኋላ እግዚአብሔር ለሴቲቱ ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም ገዢሽ ይሆናል ካለ ጊዜ ጀምሮ አንዳንድ ወንዶች አባወራነት በወንድ በኩል የመጨቈኛ ቃል በማስመሰል ይመለከቱታል፡፡ ዛሬም በአብዛኛው የዓለም ሰዎችና እንዲሁም በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ ነገሩን በዚህ መልኩ ያስተውሉታል፡፡ ስለዚህ በቀጥታ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተመልሰን እግዚአብሔር የሰጠንን ትክክለኛ ምሳሌ መመርመር ይገባናል፡፡ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ራሱን አሳልፎ እስከሚሰጥ ድረስ ፍቅሩን አስረዳ፡፡ እንዲሁም ደግሞ ባል በአባወራነቱ ሲጠቀም ከክርስቶስ ጋር በተመሳሳይ ርኅራኄና ፍቅር ሚስቱን እንዲወድዳት ሐዋርያው ጳውሎስ ያስተምራል፤  ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደደና ራሱን ስለ እርስዋ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፡፡ ይላል፡፡ ሥልጣን ኀላፊነትና ፍቅር በአባወራነት ላይ የሚታዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ከነዚህም ነገሮች ውስጥ አንዱ ቢጐድል ሁሉም ይበላሻሉ፡፡ የዚህም ውጤት በባልና ሚስት መካከል ችግር መፍጠር ነው፡፡

ሚስቲቱ አባወራነትን እንዴት ትመለከታለች?

አባወራነት ካለ መታዘዝ ይኖራል፤ አንዱ ለኀላፊነት ከታጨ ሌሎቹ ለእርሱ መታዘዝ ይኖርባቸዋል፡፡ እንግዲህ ለቤተ ሰብ ከእግዚአብሔር የተሰጠ መለኮታዊ ምሳሌ ሴት የባልዋን አባወራነት እንድትቀበልና ለእርሱም እንድትታዘዝ መሆኑን በሐዋርያ ጳውሎስ ቃል ተግልጦአል፡፡ ሚስቶች ሆይ ለጌታ ኢየሱስ እንደምትታዘዙ ለባሎቻችሁ ታዘዙ፡፡ ክርስቶስ ለአብ እንደ ታዘዘ ሚስት ለባልዋ ስትታዘዝ የጌታን መንገድ በመከተልዋ ከፍተኛ ጥሪዋን ስታከብር እናያለን፡፡ የእርስዋ ለባልዋ መታዘዝ የሚዘክረው ቤተ ክርስቲያንም በክርስቶስ እንደምትታዘዝ የሚያገለግል ምሳሌ እንደ ሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ ያስረዳናል ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትታዘዝ እንዲሁም ሚስቶች በሁሉ ነገር ለባሎቻቸው ይታዘዙ ይላል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ብዙ ባለትዳር ሴቶች በዓለም አመለካከት በማየት መታዘዝን እንደ ባርነት በመቊጠራቸው ራሳቸውን ዐርነት ያወጡ ስለሚመስላቸው ከመታዘዝ ለማምለጥ ይፈልጋሉ፡፡ ሰይጣን ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ መታዘዝን ባለመታዘዝ ለውጦአል፡፡ ይኸውም በፍቅር ለእርሱ ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ እስከሚሰጥ ድረስ ለሚወድዳት ባል በቅንጅት ውስጥ በመታዘዟ ደስ ሊላት ይገባል፡፡ ነገር ግን ሰይጣን በሴትነቷ እንደ ዕቃና እንደ ገረድ እንድትሆን ለሚቈጥር ወንድ ወደ መገዛትና ወደ ባርነት አልፋ የተሰጠች እንደ ሆነች አድርጎ ስለ ቀየረው ሚስት ለባል መታዘዟ ቅር ይላታል፡፡ ይህም እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ አይደለም፡፡ ስለዚህ ዐሳባችን በዙሪያችን በሚሰፍን ግብረ ገብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል በሚሠራ በመንፈስ ቅዱስ እንዲታነጽ ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚል አእምሮአችሁ ታድሶ ሕይወታችሁ ይለወጥ እንጂ የዚህን ዓለም ሰዎች ክፉ ጠባይ አትከተሉ፡፡ ሚስት ለባልዋ መታዘዝ ማለት በቤተ ሰብ መካከል በውይይትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ አለመካፈል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሲመካከሩ እግዚአብሔር የባልዋን ዐሳብና ፍላጎት እንዲያቀና ትማጸናለች፡፡ ሆኖም በብርቱ ነገር የዐሳብ አለመግባባት በመካከላቸው ሲከሠት ባልዋ ውሳኔ እንዲሰጥበት ዝግጁ ሆኖ ውጤቱ የቀና እንዲሆን ለእግዚአብሔር አደራውን ታስረክባለች፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ምሳሌዎች

ሣራ ከአብርሃም ጋር ወደ ሰው አገር ስትጓዝ በጣም ውብ ሴት በመሆንዋ አብርሃም ለሕይወቱ ይፈራ ነበርና፥ ሁለት ጊዜ እኅቴ ናት ብሎ ሰዎቹን ሲያታልል በዚህ ለአብርሃም ታዘዘች፡፡ አልታዘዝም አላለችውምና ምንም እንኳ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ብትገባም፥ የአብርሃምን ትእዛዝ ተቀብላ እግዚአብሔር እንደሚያድናት አመነች፡፡ እርሷ በአብርሃም ግማሽ ውሸት (በአባቱ በኩል እኅቱ ነበረችና) ባትስማማ ይሻል ነበር ብለን ብናስብ ዐዲስ ኪዳን ስለዚህ ነገር ምንም አይናገርም፡፡ ሆኖም ሣራ ለባልዋ ስለ መታዘዝዋ እያመሰገንዋት ክርስቲያኖች የሆኑ ሴቶች ሁሉ ምሳሌነትዋን አርኣያነትዋን እንዲከተሉ ያሳስባቸዋል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ  የከበረ የዋኅና ጭምት መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ፡፡ ...  እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም ጌታ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት … ውበቱ ሰዎች ከሚረዱት ይህ ቀረሽ ከማይባለው ውጫዊ የሰውነት ውበቷ እጅግ የላቀ መሆኑን ከዚህ አንቀጽ ልናስተውል እንችላለን፡፡

በአብርሃምና በሣራ መካከል የተለመደው ግንኙነት በአንድ ወቅት ለጊዜው እንደ ተበላሸ መጽሐፍ ቅዱስ ይተርካል፡፡ እግዚአብሔር ልጅ እንደሚወልዱ ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር፤ ሆኖም ሳይወልዱ ለብዙ ዓመታት ቈዩ፡፡ በዚህም ምክንያት በመካከል ሣራ የራሷን ርምጃ ለመውሰድ ፈለገች፡፡ አብርሃምም በአካባቢው የነበሩትን አረማውያን ልማድ ተከትሎ አጋር ከተባለች የሣራ አገልጋይ ልጅ እንዲወልድ ሣራ ባልዋን መከረችው፡፡ እግዚአብሔር ከሰጣት ኀላፊነት በመውጣት ይህን የመሰለ የእምነት ጒድለት በማሳየቷ የባሏ መሪ ለመሆን ሞከረች፡፡ ከዚህም በመቀጠል አብርሃም ከእርሱ ኀላፊነት ወጥቶ ሣራ ባለችው ነገር ተስማማ፡፡ የዚህም ስሕተት ውጤት እስከ ዛሬ ድረስ የሚሳዝን ሆኖ በግልጽ ይታያል፡፡ ምክንያቱም የእስራኤል ትውልድ ከሣራና ከአብርሃም በተገኘው ልጅ በይሥሐቅ በኩል ሲቈጠር የዐረብ ትውልድ ግን ከአብርሃምና ከአጋር በተገኘው በእስማኤል በኩል ሲቈጠር ይታያል፡፡

የአብርሃም ልጅ ይሥሐቅ ሚስቱን ርብቃን ፈልጎ ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ ምንም እንኳ እግዚአብሔር ሁለቱን ቢያገናኛቸውም ይሥሐቅ ግን ቤተ ሰቡን በትክክል ለመምራት ችግር ነበረበት፡፡ በዚህም ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁኔታው እየባሰ ሄዶ በመጨረሻ በአንድ ወቅት አማራጭ በሌለው ሁኔታ ላይ ወደቀ። ይሥሐቅ በሚስቱ አስተሳሰብ ሥር በመሆኑ በታናሽ ልጁ በያዕቆብ ተታለለ፡፡ ይሥሐቅ ቤተ ሰቡን ለመምራት ባለመቻሉና ሚስቱም ለእርሱ ሳትታዘዝ በራስዋ ፈቃድ ለመኖር በመሻትዋ ቤተ ሰቡም በሙሉ ለከፋ ችግር ተጋለጠ፡፡

ሔዋን ብቻዋን ስትሆን ለምን መልካምና ክፉ ወደሚያስታውቀው ዛፍ ቀረበች? ከእግዚአብሔር የተከለከለውን ፍሬ ለመወሰድ ውሳኔ ስታደርግ ምክርን ለመጠየቅ ወደ ባለቤትዋ ለምን አልሄደችም? አንድ ጊዜ ነገሩን በገዛ እጇ ከወሰደች በኋላ አዳም አባወራነቱን ስላልተጠቀመበት በእርሷ በተያዘ መሪነት ተሸነፈ፡፡ ምን ዐይነት አሰቃቂ ውጤት እንዳስከተለ ሁላችን እናውቃለን፡፡

በአባወራነት ላይ የሚነሡ ወቅታዊ ጥያቄዎች
ላገቡት፥ በጋብቻችን ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠውን አርኣያ በአግባብ እንፈጽማለንን? እኔ ባል ስሆን ከእግዚአብሔር የተሰጠኝን አባወራነት እፈጽማለሁን? የቤተ ሰቤ መሪ ሆኜ ኀላፊነቱን እወስዳለሁን? ይህን አባወራነት በእውነተኛ ፍቅር ራሴን መሥዋዕት እስከማደርግ ድረስ ለመፈጸም ዝግጁ ነኝን? ለምሳሌ ዱሮ ለሌላ ነገር የተጠቀምኩበትን ገንዘብና ሰዓት ልማዶችና ከጋብቻ በፊት የወድድኳቸውን ጓደኞች ለሚስቴ ስል ለመተው ዝግጁ ነኝን? ከዚህ በፊት ያልፈጸምኳቸውን አንዳንድ ነገሮች ለእርሷ ስል እፈጽማለሁን? የሚመቸውን ረዳት-ጓደኛ ለመቀበል አዳም ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ሔዋንም ሕይወት እንድትቀበል የአዳም ሰውነት ተሰብሮላት ነበር፡፡ ለእንደዚህ ዐይነት መሥዋዕት ዝግጁ ነኝን?

እኔ ሚስት ስሆን ለባለቤቴ በመታዘዜ ለጌታ እየሱስ እንደምታዘዝ እገልጣለሁን? ለባለቤቴ እንደ መታዘዜ የጌታ ኢየሱስን መንገድ እንደምከተል አስተውላለሁን? ከባለቤቴ ጋር በሰላም እንድኖር በቤተ ሰብ ውስጥ የዘመዶቼን ጣልቃ ገብነት ለመቈጣጠር ዝግጁ ነኝን? ስለ ልጆቻችን አስተዳደርና ስለ ገንዘባችን አጠቃቀም የባለቤቴን ውሳኔዎች ለመቀበል ዝግጁ ነኝን? በዕለት ፕሮግራማችን ላይ የእርሱን ምክር መቀበል እችላለሁን? ዋናው ቁም ነገር የሚስትነትና የእናትነት ኀላፊቴን ለመጠበቅ በእምነት የራሴን ፕሮፌሽናል ሥራ ለመተው ዝግጁ ነኝን? እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚሰጠን አምናለሁን? እግዚአብሔር በእኔ ውስጥ ደስ የሚያሰኘውን ጭምት መንፈስ እንዲፈጥር እለምነዋለሁን?

ስለ ጋብቻ ለሚያስቡ ላላገቡት ወንዶች

ወደ ፊት ስለማገባት ሚስት ሳስብና ስጸልይ ምን ብዬ ራሴን መጠየቅ ይገባኛል? ለእርስዋ ኀላፊነትንም እስከምወስድ ድረስ እወዳታለሁን? እርስዋ በደስታ እንድትታዘዝልኝ እንድትከተለኝ እኔ ለእርሷ መልካም መሪ መሆን እችላለሁን? ስለዚህ ባለመታዘዟ እኔን የማታከብር ሴት እውነተኛ ሚስት ትሆናለች ብዬ አላስብም፡፡


ስለ ጋብቻ ለሚያስቡ ላላገቡት ሴቶች፤

ወደ ፊት ስለማገባው ባል ሳስብና ስጸልይ እስከምታዘዝለት ድረስ አከብረዋለሁን? እኔ ለትዳር የምመርጠውን ወንድ እስከምታዘዝለት የማላከብረው ከሆነ ባላገባው ይመረጣል፤ ምክንያቱም ትዳራችን ውሎ ዐድሮ ችግር ላይ ይወድቃልና፡፡

በባልና በሚስት መካከል ያለው የፍቅር ግንኙነት ከእግዚአብሔር የተሰጠውን አብነት እንዲገልጥና የጋብቻችን አመሠራረትም እንደ እርሱ ፈቃድ እንዲሆን የሕይወት ቃል ለዓለም ሰዎች በማቅረብ ቤተሰቦቻችንም በእነርሱ መካከል ሆነው እንደ ሻማ እንዲያበሩ እግዚአብሔር ይርዳን!

ከመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ ጥቅሶች፤
ዘፍ. 2፥21-25፤ 3፥1-8፡16፤ 12፥10-22፤ 16፥1-4፤ 20፥1-18፤ 24፥1-4፤27፤ ማቴ. 1፥24 2፥13፡19፡22፤ ሉቃ. 1፥38፤ ሮሜ 12፥2፤ 1ቆሮ. 11፥3፤ ኤፌ. 5፥23-25፤ ፊል. 2፥15፤ 1ጢሞ. 2፥13፡፡

No comments:

Post a Comment