Sunday, September 20, 2015

ኢየሱስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ

ስለ ጌታችን፥ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት ባለፉት ተከታታይ ዕትሞች ትምህርቶች ሲተላለፉ ቈይተዋል። ዛሬ የመጨረሻውን ክፍል የምንመለከት ሲሆን፥ “የክርስቶስ መካከለኛነት በሥጋ ወደሙ በኩል የሚፈጸም ነው” የሚለውን የአንዳንዶች አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመመርመር እንሞክራለን። በርግጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ “ክርስቶስ መካከለኛ ነው ማለት ሥጋ ወደሙ መካከለኛ ነው ማለት ነው” ብላ እንደምታስተምር በግልጥ የተጻፈ ነገር አልተገኘም። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚሰብኩ አንዳንድ ሰባክያን ግን ትምህርቱን ባፍም በመጣፍም ሲያስተምሩት መገንዘብ ችለናል።

መምህር ታሪኩ አበራ የተባሉ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቅ “ኢየሱስ ማነው?” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፥ “ዛሬ ኢየሱስ ለእኛ ጠበቃ ነው ስንል በሰማይ ከዲያብሎስ ጋር፥ ዕለት በዕለት የሚጨቃጨቅ የሚከራከር ጠበቃ ሆኖ አይደለም፤ አንድ ጊዜ በፈጸመው የማዳን ሥራ የጌታን ሥጋና ደም ከተቀበልን … ያ ሥጋና ደም … ጠበቃ ሆኖ ከዲያብሎስ ክስ ነጻ ያወጣናል። ለዚህ ነው ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው ያለው” ሲሉ ጽፈዋል (ገጽ 119 አጽንዖት የግል)። እርሳቸው እንዲህ ያሉት፥ “ልጆቼ ሆይ፥ ኀጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (1ዮሐ. 2፥1) ለሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ማብራሪያ እሰጣለሁ ብለው ነው።በተመሳሳይም መምህሩ፥ “እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል” (ዕብ. 7፥25) ለሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ማብራሪያ ሲሰጡም የሚከተለውን ጽፈዋል፤ “ዛሬ የምንሠዋው መሥዋዕት /ሥጋ ወደሙ/ ከዕለተ አርቡ ጋር አንድ ስለ ሆነ ዘወትር ሲያስታርቀን ይኖራል ማለት ነው።” (ገጽ 144 አጽንዖት የግል)። እርሳቸው ይህን ሐሳብ በጽሑፍ ያስፍሩት እንጂ ብዙዎች በቃል ሲናገሩት በተደጋጋሚ ተደምጧል።

የትምህርቱ ምንጭ ምን ይኾን?
ወደ ዕብራውያን ሰዎች በተጻፈው መልእክት ውስጥ፥ “… የዐዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚኾን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል” (ዕብ. 12፥24) የሚለው ንባብ፥ አንዳንዶች፥ “ሥጋ ወደሙ መካከለኛ ነው” እንዲሉ በር እንደ ከፈተላቸው ይገመታል። ይህ ጥቅስ ግን ስለ ሥጋ ወደሙ ሳይሆን በቀራንዮ ስለ ፈሰሰው የክርስቶስ ሕያው ደም የተነገረ ነው፤ ከአቤል ይልቅ የሚሻለውን የሚናገር የመርጨት ደም የተባለው እርሱ ነውና።

“የመርጨት ደም” አስቀድሞ እስራኤል ከግብጽ በወጡበት በዚያ ሌሊት፥ ሞተ በኵር እንዲያልፋቸው ፋሲካውን ዐርደው ደሙን በቤታቸው መቃንና ጕበን ላይ በመቅባት ያከናወኑትን ሥርዐት የሚያስታውስ ነው (ዘፀ. 12፥7)። ይህን በግዘፍ የተከናወነውን የፋሲካውን ደም መረጨት፥ የዕብራውያኑ ጸሓፊ፥ “ሙሴ … አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ” በማለት ገልጦታል (ዕብ. 11፥28)። ክርስቲያኖችም ወደዚህ የመርጨት ደም እንደ ደረሱና ይህ የመርጨት ደም ከአቤል ደም ይልቅ የሚሻለውን የሚናገር መሆኑን ጨምሮ ጽፏል። “የሚሻለውን የሚናገር” የተባለው ምንድን ነው? የአቤል ደም ወደ እግዚአብሔር የጮኸው ገዳዩን ወንድሙን ለመክሰስ እንደ ሆነ ግልጥ ነው (ዘፍ. 4፥10)። የክርስቶስ ደም ግን በግዘፍ ሳይሆን በመንፈስ የተረጨና በእርሱ በኩል አምነው የሚመጡ ሁሉ የኀጢአታቸውን ስርየት የሚቀበሉበት ሕያውና ነባቢ (የሚናገር) ደም ነው፤ የሚከስ ሳይሆን የሚያስታርቅ ደም ነው፤ ከሳሽ ቢነሣም የሚከራከር ክቡር ደም ነው።

ሐዋርያው ጴጥሮስ መልእክት የጻፈላቸውን ክርስቲያኖች፥ “… እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት …” በማለት ነበር የገለጣቸው (1ጴጥ. 1፥1-2)። በርግጥም እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ክርስቲያኖች ኹሉ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ያወቃቸው፥ በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሱ፥ ለመታዘዝና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ለመረጨት የተመረጡ ሰማያዊ ዜጎች ናቸው። የመርጨት ደም የተባለውም የክርስቶስ ደም ሲሆን፥ እርሱም በግዘፍ ሳይሆን በእምነት የተረጨውን ሰው ከኀጢአቱ እንደሚያነጻ ያሳያል። በሌላም ስፍራ መጽሐፍ ቅዱስ፥ “የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል” ይላል (1ዮሐ. 1፥7)። ደግሞም “እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን” በማለት ይመሰክራል (ሮሜ 5፥9)።

ከላይ በተገለጠው እውነት ላይ ተመሥርቶም መጽሐፈ ቅዳሴ እንዲህ ይላል፤ “ወናሁ ደመ መሲሕከ ንጹሕ ዘተክዕወ በእንቲኣየ በቀራንዮ ይኬልሕ ህየንቴየ ዝንቱ ደም ነባቢ ይኩን ሰራዬ ኀጢአትየ ለገብርከ። - ስለ እኔ በቀራንዮ የፈሰሰ ንጹሕ የሚሆን የመሢሕም ደም እነሆ ስለ እኔ ይጮኻል። ይህ የሚናገር ደም የእኔን የባሪያህን ኀጢአት የሚያስተሰርይ ይሁን” (መጽሐፈ ቅዳሴ ገጽ 54)። ምንም እንኳ ይህ ምስክርነት የተነገረው በመጽሐፈ ቅዳሴ ላይ ስለ ሆነ ነገሩን ከሥጋ ወደሙ ጋር ለማያያዝ የተመቸ ቢመስልም፥ የዚህ ምስክርነት መሠረቱ ከላይ የተጠቀሰው ዕብ. 12፥24 በመሆኑ፥ ወደ ክርስቶስ ሕያው ደም ነው የሚመራው (ስለዚህ ጕዳይ በጮራ መጽሔት ቍጥር 8 ገጽ 30 ላይ የቀረበውን ጽሑፍ መመልከት ይቻላል)።

እስካሁን እንደ ተመለከትነው፥ “ከአቤል ደም ይልቅ የሚሻለውን የሚናገር” የተባለው አንድ ጊዜ በቀራንዮ የፈሰሰውና ክርስቶስ ወደ ሰማያዊቱ ቅድስተ ቅዱሳን ይዞት የገባው ደሙ (ዕብ. 9፥12፤ 13፥12) ነው እንጂ፥ ለሞቱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ በተያዘባት በዚያች ሌሊት ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ሥጋ ወደሙ አይደለም። ስለዚህ “ሥጋ ወደሙ መካከለኛ ነው” የሚለው ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ትምህርት እንደ ሆነ መናገር ይቻላል።    

በክርስቶስ ሕያው ደምና በሥጋ ወደሙ መካከል ያለው ልዩነትና ኅብረት
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ አርብ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ሕያው ደምና ለሞቱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በስቅለቱ ዋዜማ በምሴተ ኀሙስ (ኀሙስ ማታ) ለደቀ መዛሙርቱ ‘ሥጋዬ እና ደሜ ነው’ ብሎ በሰጣቸው ኅብስትና ወይን መካከል ኅብረትም ልዩነትም እንዳለ ማወቅ አስፈላጊ ነው። አሊያ ትልቅ መደናገር ይፈጠራል። መጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱን አስተባብሮም፥ አለያይቶም የገለጠበት ሁኔታ አለ።

የክርስቶስ ደም ስለ በደላችን አንድ ጊዜ የፈሰሰ፥ በግዘፍ ሳይሆን በርቀት (‘ቀ’ ጠብቆ ይነበብ)፥ በሚታይና በሚዳሰስ ሳይሆን በእምነት ያዳነን ክቡር ደም ነው። አንድ ጊዜ ስለ እኛ የፈሰሰው ይህ የክርስቶስ ደም፦
·        ከከንቱ ኑሯችን የተዋጀንበት (1ጴጥ. 1፥18-19፤ ሐ.ሥ. 20፥28፤ ኤፌ. 1፥7)
·        ከኀጢአታችን የታጠብንበት (ራእ. 1፥4-5፤ 7፥14)
·        ኀጢአታችን የተሰረየበትና የሚሰረይበት (ኤፌ. 1፥7፤ ሮሜ 3፥25)
·        ወደ እግዚአብሔር የቀረብንበት (ኤፌ. 2፥13)
·        ወደ እግዚአብሔር ለመግባት ድፍረት ያገኘንበት (ዕብ. 10፥19-20)
·        የጸደቅንበት (ሮሜ 5፥9)
·        የተቀደስንበት (ዕብ. 9፥14፤ 13፥12)
ክቡርና ሕያው ደም ነው። እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች ሥጋ ወደሙን ሳይሆን አንድ ጊዜ የፈሰሰውንና በእምነት የተቀበልነውን የክርስቶስን ሕያው ደም የሚያሳዩ ናቸው።

ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ እንጂ፥ ሥጋ ወደሙን መሥዋዕት አድርጎ አላሳረገም (ኤፌ. 5፥2፤ ዕብ. 9፥14)። ሥጋ ወደሙን ባርኮ፥ ቈርሶና አመስግኖ እንዲበሉትና እንዲጠጡት የሰጠው ለደቀ መዛሙርቱ ነው (ማቴ. 26፥26-27፤ ማር. 14፥22-23)። ደቀ መዛሙርቱንም በሥጋ ወደሙ የእርሱን መታሰቢያ እንዲያደርጉና ጌታ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን እንዲናገሩ አዘዛቸው (ሉቃ. 22፥19፤ 1ቆሮ. 11፥24-26)። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ይህን ትእዛዝ በመፈጸም መታሰቢያውን እያደረገችና ማሕየዊ (የሚያድን) ሞቱን እየተናገረች ትገኛለች፤ ጌታ ዳግም እስኪመጣ ድረስም እየተናገረች ትቀጥላለች።
                                                
በመስቀል ላይ ስለ ኀጢአታችን አንድ ጊዜ የፈሰሰውና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማያዊቱ ቅድስተ ቅዱሳን ይዞት የገባው ሕያው ደሙንና ዳግም እስኪመጣ ድረስ ሞቱን እየተናገሩ መታሰቢያውን እንዲያደርጉበት በሐዋርያት በኩል ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠው ሥጋ ወደሙን በየራሳቸው የገለጠበት ሁኔታ እንዳለ ሁሉ፥ እርስ በርስ ያላቸውን ኅብረት ያሳየበትም ሁኔታ አለ። ጌታ በተያዘባት ሌሊት ሥጋ ወደሙን ለደቀ መዛሙርቱ ሲሰጣቸው፥ እንጀራውን “ይህ ሥጋዬ ነው” ብሏል (ማቴ. 26፥26፤ ማር. 14፥22፤ ሉቃ. 22፥19፤ 1ቆሮ 11፥24)። ጽዋውንም አንሥቶ ይህ ጽዋ፥ “ስለ ብዙዎች ለኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የዐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” ማለቱ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፏል (ማቴ. 26፥28፤ እንዲሁም ማር. 14፥24፤ ሉቃ. 22፥20፤ 1ቆሮ 11፥25)። ይህም የሚያሳየው አንድ ጊዜ በፈሰሰው የክርስቶስ ሕያው ደምና ለሞቱ መታሰቢያ እንዲሆን ለደቀ መዛሙርቱ በተሰጠው ሥጋ ወደሙ መካከል ኅብረት ያለ መሆኑን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያስረዳ ለቆሮንቶስ ምእመናን በጻፈው የመጀመሪያ መልእክቱ ላይ እንዲህ ብሏል፤ “የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?” (1ቆሮ. 10፥16)።

ሥጋ ወደሙ ለምን ተሰጠ?
ሥጋ ወደሙ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠበትን ምክንያት ከላይ በተነሣው ነጥብ ውስጥ ለማሳየት ተሞክሯል። ራሱ ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተናገረው፥ ሐዋርያው ጳውሎስም ከእርሱ የተቀበለውን እንዳስተላለፈልን (1ቆሮ. 11፥23)፥ ጌታችን ሥጋ ወደሙን ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው፥ የሞቱን መታሰቢያ እንዲያደርጉበትና ዳግም ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ማሕየዊ ሞቱን እንዲናገሩ ለማድረግ ነው። በዚህ ዐላማ መሠረት ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም የተሰጠው ሥጋ ወደሙ የሚያስገኛቸው መንፈሳውያን በረከቶች እንዳሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንማራለን። እነርሱም፦

·        የሞቱን መታሰቢያ በሥጋ ወደሙ ስናደርግ፥ ነፍሱን አሳልፎ እስከ መስጠት በመድረስ የገለጠውን የክርስቶስን ወደር የለሽ ፍቅር ከሌላው ጊዜና አጋጣሚ በበለጠ በጥልቀት እንድናስብ ትልቅ ዕድል ይፈጥርልናል።  
·        በእንጀራና በጽዋ (በኅብስትና በወይን) የተሰጠው ሥጋ ወደሙ ከክርስቶስ ሥጋና ደም ጋር ኅብረት ያለው በመሆኑ፥ ሥጋ ወደሙን በምንቀበል ጊዜ ከክርስቶስ ጋር የሚኖረን ኅብረት ይጠናከራል (1ቆሮ. 10፥16)።
·        ከሥጋ ወደሙ የምንቀበል አንዱን እንጀራ የምንካፈል እንደ መሆናችን ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ መሆናችንን እንመሰክርበታለን፤ ይህም እርስ በርሳችን ለሚኖረን ኅብረት አስፈላጊ ነው (1ቆሮ. 10፥17፤ ሐ.ሥ. 2፥41፡42)።
·        ንስሓ ሳይገቡ ሥጋ ወደሙን መቀበል ፍርድን ያመጣልና ሥጋ ወደሙን ስንቀበል ራሳችንን እየመረመርን ስለሚሆን፥ ከኀጢአት እንድንርቅና ራሳችንን እየመረመርን በቅድስና እንድንኖር ይረዳናል (1ቆሮ. 10፥21-22፤ 11፥27-31)።

ከነዚህና ከመሳሰሉት ውጪ ሥጋ ወደሙ የተሰጠበት ሌላ ዐላማ እንዳለ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ሆኖም ሥጋ ወደሙ ከዚህ ውጪ ለሆኑ ጕዳዮች እንደ ተሰጠ ተደርጎ የሚወሰድባቸው ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ሁለቱን ቀጥሎ እንመለከታለን። የመጀመሪያው፥ ሥጋ ወደሙ ለጋብቻ ማኅተምና ሁለቱ ጥንዶች እንዳይለያዩ ማሰሪያ ተደርጎ መወሰዱ ነው። ሥጋ ወደሙ ‘በአማኞች መካከል ኅብረት እንዲጠናከር ያድርጋል’ የሚለውን ለጥጠን በጋብቻ ቀንበር የተጠመዱትን ባልና ሚስት ኅብረትም ያጠናክራል ካላልን በቀር፥ ሥጋ ወደሙ ለጋብቻ ማኅተምና ማሰሪያ እንዲሆን የተሰጠበትን ሁኔታ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም።

ጋብቻ እንዲጣመሩ ፈቃደ እግዚአብሔርን ባገኙና ተዋድደው ለሕይወት ዘመን ጕድኝት በተስማሙ አንድ ወንድና አንዲት ሴት መካከል የሚፈጠር ቅዱስ ኅብረት ነው። የዚህ ኅብረት መሠረትና ማኅተም የእግዚአብሔር ፈቃድና በመካከላቸው ያለው ፍቅር ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ሳይኖሩ ሥጋ ወደሙን ማኅተምና ማሰሪያ አድርጎ ጋብቻን መፈጸም፥ ሩቅ ዐላሚ የሆነውን ቅዱስ ጋብቻ በቅርቡ ማሳደር ይሆናል። በዚህ መንገድ ጋብቻቸውን የፈጸሙና ብዙም ሳይቈይ ጋብቻቸው በፍቺ የተደመደመውን ቤቱ ይቍጠረው።

ከዚህ የተነሣ በሥጋ ወደሙ የሚፈጸምን ጋብቻ እንደ ጦር የሚፈሩት ጥቂቶች አይደሉም። ብዙዎች በሥጋ ወደሙ የሚፈጸምን ጋብቻ እንዲፈሩት እያደረገ ያለው፥ የትዳር አጋሮቻቸው በፈቃደ እግዚአብሔር እንዳላገኟቸው በማሰብና በፍቅር ይዘው እንደማያቈዩአቸው በመገመት በሥጋ ወደሙ ገመድ ለማሰር የመፈለጋቸውና እነርሱም ሥጋ ወደሙ ለዚህ ዐላማ የተሰጠ ማሰሪያ ገመድ አድርገው ስለ ቈጠሩት እንደ ሆነ ይታመናል። ስለዚህ ብዙዎች ከጋብቻ ጋር በተያያዘም ሆነ በቀጥታ ሥጋ ወደሙን የሚሸሹት፥ ሥጋ ወደሙ የተሰጠበት መጽሐፍ ቅዱሳዊና ትክክለኛ ዐላማው ስላልገባቸውና በሌላ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱት ስለ ተደረገ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ከላይ የተዘረዘሩትን መንፈሳውያን በረከቶች የምናገኝበት መሆኑን ቢያስተውሉ ግን አመለካከታቸው ይለወጣል።
 
ሌላው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነውና ልማዳዊ የሚመስለው ልምምድ፥ ሥጋ ወደሙ በጽኑ ደዌ የተያዘ ሰው ሥጋ ወደሙ ቢቀበል ይድናል ወይ ይሞታል የሚለው ነው። ይህም ልማድ በሥጋ ወደሙ የክርስቶስን ሞት ማሰብ ከሚለው ሐሳብ በእጅጉ የራቀ ነው። ሥጋ ወደሙ ራሳቸውን መርምረው ለሚቀበሉት ብዙ በረከት ሲያስገኝ፥ በኀጢአት ሆነው ወይም ንስሓ ሳይገቡ በሚቀበሉት ላይ ደግሞ ደዌንና እስከ ሞት የደረሰ ተግሣጽን ያመጣባቸዋል (1ቆሮ. 11፥27-32)። ሆኖም ክርስቲያን በጽኑ ደዌ በተያዘ ጊዜ ጌታ እንዲፈውሰው መጸለይ እንጂ በሥጋ ወደሙ እንዲድን ወይም እንዲሞት አሳልፎ መስጠት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።   

ሥጋ ወደሙ መካከለኛ ነው ማለት ለምን አስፈለገ?
ወደ ቀደመው ነገር እንመለስ፤ ክርስቶስ መካከለኛ ነው ማለት ሥጋ ወደሙ መካከለኛ ነው ማለት ነው የሚለውን እንግዳ ትምህርት እያስተማሩ ያሉ ክፍሎች፥ የክርስቶስን መካከለኛነት በሥጋ ወደሙ “መካከለኛነት” መተካት ለምን ፈለጉ? የሚለው ጥያቄ መጠየቅና ምላሽ ማግኘት አለበት። በቅድሚያ ሥጋ ወደሙ መካከለኛ ነው የሚል ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛ አንድ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን ነው የሚናገረው (1ጢሞ. 2፥5፤ ዕብ. 9፥15፤ 12፥24)።

‘ሥጋ ወደሙ መካከለኛ ነው’ የሚለውን ይህን ትምህርት ወደ ማስተማር የተገባው በዋናነት ስለ ክርስቶስ መካከለኛነት የሚናገሩትን መጽሐፍ ቅዱሳውያን ክፍሎች እንዳላዩ ሆኖ ማለፍ፥ ወይም በግእዙ ገጸ ንባብ መሸፈንና ትርጕሙን ማዛባት፥ አሊያም ሌሎች ምክንያቶችን ደርድሮ ከጥቅሶቹ መሸሽ ብዙም እንደማያዋጣ ስለ ታመነበት ነው ብንል ከእውነታው አልሸሸንም። ይሁን እንጂ አሁንም ኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛ ማድረግ ለእነዚህ ወገኖች ትክክለኛ ትምህርት መስሎ ስለማይታያቸው ክርስቶስን በቀጥታ መካከለኛ ከማድረግ፥ መካከለኛነትን ለሥጋ ወደሙ ብንሰጥ የተሻለ ይሆናል፤ እርሱን በቀጥታ መካከለኛ ከማለትም ያድነናል በሚል ስሌት ወደዚህ እንግዳ ትምህርት ሄደዋል ማለትም ይቻላል። እንዲህ በማድረጋቸው በአንድ በኩል ኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛ መሆኑን የሚናገሩ መጽሐፍ ቅዱሳውያን ጥቅሶችን እኛም እንጠቅሳቸዋለን ለማለት አመቺ ሆኖላቸዋል። በተጨማሪም ጥቅሶቹን ለሥጋ ወደሙ በመስጠት ኢየሱስ መካከለኛ ነው የሚለውን ትምህርት ለማስተባበል ይጠቀሙበታል።

ነገር ግን ይህ ትምህርት አደገኛ ነው፤ ምክንያቱም፥ መጽሐፍ ቅዱስና የጥንት አባቶች መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው ያስተማሩትን የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት ላለመቀበል የተደረገ ጥረት ተደርጎ ሲወሰድ፥ የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት ዐሌ ብሎ ሥጋ ወደሙን (ቅዱስ ቊርባንን) መካከለኛ ማድረግም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ እንግዳ ትምህርት ማስተማር ይሆናል።   

ማጠቃለያ
ከጮራ ቍጥር 39 ጀምሮ እስከዚህ ዕትም ስለ ዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት በተከታታይ ትምህርቶች ተሰጥተዋል። ትምህርቶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ፥ አበውም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው ያስተማሯቸው ናቸው። ከዚህ በተቃራኒ ይህን እውነት ለማስተባበል እየተሰጡ የሚገኙ የስሕተት ትምህርቶችንም በንጽጽር ለማሳየት ሞክረናል። በዚህ መንገድ እየቀረቡ ያሉት ማስተባበያዎች፦ መጽሐፍ ቅዱስ በልዩ ልዩ መንገድ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት የተናገራቸውን መልእክቶች በመሸሽና ሌላ ትርጉም በመስጠት፥ ስለ መካከለኛነቱ የሚናገሩ ጥቅሶችን የእኛ እንዳልኾኑ በመቍጠር፥ የክርስቶስን መካከለኛነት በቅዱሳን ሰዎችና መላእክት “መካከለኛነት” በመተካት፥ ወዘተ. የተመሠረቱ መሆናቸውን ለማየት ጥረት ተደርጓል። በዚህም የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንጂ ሌላ መካከለኛ ከሰውም ከመላእክትም ወገን የሌለ መሆኑን ከቀረቡት ትምህርቶች ግንዛቤ ተወስዷል የሚል እምነት አለን። ከእግዚአብሔር ጋር ለታረቅንበት መካከለኛችን፥ አምላክም ሰውም ለሆነው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ይሁን፤ ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን። 

1 comment: