Thursday, November 6, 2014

ርእሰ አንቀጽ

“ንፈቅድ ንርአዮ ለእግዚእ ኢየሱስ - ጌታ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን” (ዮሐ. 12፥21)
ከግሪክ ወደ ኢየሩሳሌም ለፋሲካ በዓል መጥተው የነበሩ የግሪክ ሰዎች ለሐዋርያው ፊልጶስ ያቀረቡት ሐሳብ ነው። ፊልጶስም ለእንድርያስ ነግሮት ኹለቱም ለኢየሱስ መጥተው የሰዎቹን መሻት አወሩለት። ጌታም፥ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” አለ። በዚህ መስተጋብር ውስጥ በተለይ ኢየሱስን ማየት የሚፈልጉ ሰዎችንና ለእነርሱ ኢየሱስን ማሳየት የቻሉ አገልጋዮችን መመልከት እንችላለን።

ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኢየሱስን የሚፈልጉና ኢየሱስን ከፈላጊዎቹ ጋር የሚያገናኙ ምን ያኽል ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ማንሣት ይኖርብናል። በዚህ ዘመን በቤተ ክርስቲያን እየታየ ያለው አንዱ ችግር፥ ጌታ ኢየሱስን የሚፈልግ ምእመንና እርሱን የሚያሳይ አገልጋይ ቍጥር እየተመናመነ መምጣቱ ነው። ርግጥ የምእመናን የልባቸው መሻትና የነፍሳቸው ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ብዙዎቹ አገልጋዮች ግን ዕረፍተ ነፍስ ወደ ኾነው ጌታ ምእመናኑን ማድረስ ሲገባቸው ወደ ራሳቸው ይስቧቸዋል። በዚህ ምክንያት ምእመናን የክርስቶስ ተከታዮች ሳይኾኑ የእነርሱ ተከታይና አድናቂ እንዲኾኑ፥ ክርስቶስን ሳይኾን እነርሱን እንዲመለከቱ፥ የሕይወታቸው ዋና ምሳሌም ክርስቶስ ሳይኾን አገልጋዮቹ እንዲኾኑ በማድረግ፥ ኢየሱስን ፈልገው የመጡትን ምእመናን ወደ ኢየሱስ ሳያደርሷቸው እነርሱ ዘንድ በማስቀረት የእነርሱ ሎሌ ያደረጓቸው አገልጋዮች ጥቂቶች አይደሉም። 

እንጠብቀዋልን ብለው ከጌታ በዐደራ የተቀበሉትን መንጋ የራሳቸው የግል ንብረት በማድረግ በተሳሳተ መንገድ ስለ መሩት፥ ብዙው ምእመን ወደ ቤተ ክርስቲያንም ኾነ ወደ መንፈሳውያን ጉባኤዎች የሚኼደው ክርስቶስን ለማየት ሳይኾን ተከታዮቻቸው ያደረጓቸውን አገልጋዮች ለማየትና ለእነርሱ ለመገበር ይመስላል። ይህ ለምእመናን ትልቅ ኪሳራ ለአገልጋዮቹም ከባድ ቅጣትን የሚያስከትል ዐደራ በልነት ነው።

ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ብቻ ሙሽራ ናት። ዘወትር ልትፈልግና ልትሻ የሚገባት ውዷን ኢየሱስን ብቻ መኾን አለበት። ጌታ ለሙሽራው ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን የሰጠው ለቤተ ክርስቲያኑ እንጂ ለአገልጋዮቹ ጥቅም እንዳልኾነም ሊታወቅ ይገባል። አገልጋዮቹ በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲሠለጥኑባት፥ ትልቅ ስምና ዝናን እንዲያገኙ፥ እንዲበለጽጉና የመሳሰለውን ምድራዊ ትርፍ እንዲያተርፉ አይደለም። ቃሉ እንደሚመሰክረው፥ ጌታ አገልጋዮችን ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው፥ “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መኾን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚኾን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይኾኑ ዘንድ” ነው (ኤፌ. 4፥12-13)። ስለዚህ አገልጋዮች ይህን ተረድተው ለተሰጣቸው ተልእኮ መፋጠንና ኀላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው።

ምእመናንም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የእነርሱ መጋቢዎች እንጂ አምላኮቻቸው እንዳልሆኑ ዐውቀው እንደ እግዚአብሔር ቃል የሆነውን ትምህርታቸውን ሊቀበሉ፥ የሕይወታቸውን መልካም ምሳሌነት ሊከተሉ፥ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከቱ በእምነታቸው ሊመስሏቸው ይገባል። ከዚህ ዐልፈው እነርሱን በማክበር ስም ከማምለክ ያልተናነሰ ተግባር በመፈጸም የመጥፎ ሥራቸው ተባባሪ መኾን የለባቸውም። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኢየሱስን የሚሹ ምእመናን ኢየሱስን የሚያሳዩ አገልጋዮች በእጅጉ ያስፈልጋሉ።

ዐዲሱ ዓመት ጌታን የምንፈልግበት ጌታን የምናሳይበት ዓመት ይሁንልን
(በጮራ ቍጥር 46 ላይ የቀረበ)

No comments:

Post a Comment