Wednesday, January 18, 2012

መሠረተ እምነት

Read Pdf
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩ ምእምናን ሲጽፍ እንዲህ አለ፡- “ስለዚህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጎችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች ናችሁ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡ በሐዋርያትና በነቢያትም መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑም ራስ የሆነው ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሕንጻው በሙሉ በእርሱ ተገጣጥሞ የጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን ያድጋል፡፡ እናንተም እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚያድርበት ሕንጻ ለመሆን በክርስቶስ ትታነጻላችሁ፤” (ኤፌ. 219-22)፡፡

ለአንድ ምእመን የማእዘኑ ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ በሆነበት፥ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ በሚያስተማምን ሁኔታ ጸንቶ መቆሙን ከሌሎች ምእመናን ጋር በመገጣጠም ለሕንጻው እድገትና ውበት አስተዋጽኦ ማድረጉን መርምሮ ከማረጋገጥና በዚህም እግዚአብሔርን ከማመስገን የሚበልጥበት ምንም ነገር እንደማይኖር የታመነ ነው፡፡


ስለዚህ የቅዱሳን ቤተ መቅደስ ሕንጻ እድገትና ውበት ለመቈጣጠር መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት መስጠት አስፈልጓል፡፡

ክፍል አንድ
ምስጢረ ሥላሴ

በሦስት የአካላት ምልአትና በአንድ የመለኮት ጽንዓት የታወቀው የአምላክ መገለጽ ለምን ምስጢር ተባለ? በፍልስፍና የተደረሰበት ምስጢር ነውን? ምእመናን ሁሉ እንዳያውቁት፥ ጥቂት የበቁ ወይም በትምህርተ መለኮት የበሰሉ ምሁራን ብቻ እንዲረዱት በአምላክ ተወስኖአልን?

አይደለም! ማንም እንዲረዳውና በእምነት እንዲቀበለው አምላክ በቃሉ ውስጥ በሦስትነትና በአንድነት ራሱን ሲገልጽ ኖሮአል፡፡ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርን ቃል በመንፈስ ለመረዳት ቅንነትና በጐ ፈቃድ ለሌላቸው ፍጥረታውያን ሰዎች በመንፈስ ግልጽ ሆኖ የታወቀው የአንድ እግዚአብሔር ሦስትነት ምስጢር ሆኖባቸው መኖሩ ሊካድ አይገባውም፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እየተባለ የተነገረው (ማቴ. 2820፤ 2ኛቆሮ. 1314) በቈጠራ ማንም ሰው ሊረዳው የሚችል የሦስት /3/ መለኮታውያን አካላት ስም ነው፡፡ ይህንኑ በመቀበል ሥላሴ /ሦስት/ የሚለው ቃል ሕያው ነፍስ የሆነውን ሰው አእምሮ የሚያደናግር ባልሆነ ነበር፡፡ እንዲህ ግልጽ የሆነው የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ሥላሴ /ሦስት/ መባል ለአንዳንዶች ገና ያልተከሠተላቸው መሆኑ አያስደንቅምን? “ምስጢረ ሥላሴ” ያሰኘውስ ይህ ሳይሆን ይቀራል!

ማስገንዘቢያ፡-  ሥላሴን በመካድ ከሰባልዮሳውያን /1/ ቀጥሎ የሚታወቁት አርዮሳውያን /2/ እግዚአብሔር በማለት በግእዝና በአማርኛ የሚጠራው መለኮታዊ ስም እንደ ዕብራይስጡ “ይሆዋ ወይም ያህዌ” መባል አለበት የሚል አቋም በመያዝ ስለ ተነሡ፥ በዚህ ስም አንተርሰውና አስታከው የሚነዙትን ሐሰተኛ ትምህርት ከመሠረቱ ጀምሮ ለማፈራረስ ሲባል በዚህ ርእስ በሚቀርበው መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት “ይሆዋ ወይም ያህዌ” የሚለውን ቃል መጠቀም የቃላት መደናገርን ያስወግዳል ተብሎ ታምኖበታል፡፡


ምዕራፍ አንድ

ይሆዋ በሦስት አካላት ራሱን ስለ መግለጹ ሰባልዮሳውያንና አርዮሳውያን በሦስት አካላት ራሱን የገለጸውን አንዱን ይሆዋ በመካድ፥ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ አንድ አካል ብቻ የሆነ ሌላ ይሆዋን በድፍረታቸው ፈጥረዋል፡፡ እንዲህም ሲሉ ይጽፋሉ፡- “ሥላሴ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ባይገኝም እንኳ ብዙ የስመ ክርስቲያን ሃይማኖቶች አምላክ ሥላሴ ነው ብለው ያስተምራሉ፡፡ … በዘመናችን አቈጣጠር በስምንተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የአትናቴዎስ እምነት አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሦስቱም ዘላለማውያን … ሦስቱም ሁሉን የሚችሉ ናቸው ብሎ ይናገራል፡፡ … ይህ መሠረተ ትምህርት በዕብራውያን ነቢያትና በክርስቲያን ሐዋርያት ዘንድ የታወቀ አልነበረም፡፡” በማለት ይሰብካሉ፡፡/3/

በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸው እውነተኛ ትምህርት በድቡሽት ላይ የቆመውን የሰባልዮሳውያንንና የአርዮሳውያንን ትምህርተ ሃይማኖት ከመሠረቱ ስለሚያፈራርሰውና እንዳልነበረ ስለሚያደርገው፥
  1. የሚከተሉትን ነጥቦች /ጭብጦች/
  2. ለየጭብጦቹ በማስረጃነት ከእግዚአብሔር ቃል የቀረቡትን ጥቅሶች እና
  3. እንደ ማስገንዘቢያ እንዲያገለግሉ በስተመጨረሻ የሠፈሩትን ማጠቃለያ ሐሳቦች በጥንቃቄ እንመርምራቸው፡፡

ነጥብ/ጭብጥ/ አንድ

የብሉይ ኪዳን አባቶችና ነቢያትም ሆኑ የአዲስ ኪዳን ሐዋርያት ይሆዋ አንድ ነው ሲሉ ብዛትን በሚያዋሕድ መለኮት አንድ መሆኑን ለመግለጽ ካልሆነ በቀር አንድ አካል ነው ለማለት ከቶ አልተጠቀሙበትም፡፡

ማስረጃ 1

  1. ኦሪት ዘፍጥረት 11 “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን” ፈጠረ ይላል፡፡ ብሉይ ኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ በተጻፈበት በዕብራይስጥ በዚህ ጥቅስ እግዚአብሔር ተብሎ የተገለጸው ስም የአንድ መለኮታዊ አካል መግለጫ የሆነ ስም አይደለም፡፡ የአንድ አካል መግለጫ ስም በሆነው “ኤል” /መላክ ወይም አምላክ/ በማለት ፈንታ “ኤሎሂም” አማልክት ተብሎ ብዛትን እንዲያመለክት ሆኖ መጻፉን የቋንቋው ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ /4/

ይህ ጥቅስ  ከዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ወደ አማርኛ ሲገለበጥ ቃል በቃል ተተርጉሞ ቢሆን ኖሮ “አማልክት በመጀመሪያ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ባሰኘ ወይም በተሰኘ ነበር፡፡

ሰባልዮሳውያንና አርዮሳውያን በአንድ ይሆዋ የሦስት መለኮታውያን አካላትን መኖር ለማስካድ የሚያበቃ መንገድ የተገኘ እየመሰላቸው “አማልክት /ኤሎሂም/ በመጀመሪያ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በሚለው የብዙ ቁጥር መግለጫ የሆነው ስም እንዲገባ ስለ መደረጉ ልዩ ልዩ የስላች ትርጉሞችን ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡ ከስላች ትርጉሞቹ ዋና ዋናዎቹን እንያቸው፡፡
ሀ/ ኤሎሂም /አማልክት/ መባሉ ለአክብሮት ነው ይላሉ፡፡ ቃሉን ለአክብሮት ይገለገሉበት የነበረ መሆኑ /5/ ቢታመንም በዚህ ጥቅስ ውስጥ እንደዚህ በሆነ ትርጉም ቃሉን ለመረዳት መሞከር ለመሸሽ እንጂ የክርክሩ /የጠይቅ … ላስረዳ/ ፍልሚያ አያዋጥም፡፡
-   በዚህ መጽሐፍ /ዘፍጥረት 3፥22/ “ይሆዋ አምላክ … አዳም ከእኛ አንደ አንዱ ሆኖአል አለ” በማለት ተጽፎአልና፡፡
-   በተጨማሪም በዚሁ መጽሐፍ 11፥5-7 “ይሆዋ … ኑ፥ እንውረድ … ቋንቋቸውንንም እንደባልቀው አለ” የሚለው የዳኝነት ውሳኔ ተመዝግቦ ይገኛልና፡፡ እነዚህና የመሳሰሉት ጥቅሶች የሰባልዮሳውያንንና የኦርዮሳውያንን የመሸሻ መንገድ ይዘጉባቸዋል፡፡ ኤሎሂም ለሚለው ስም ተለዋጭ ሆኖ የቀረበው ተውላጠ ስም “እኛ” የሚል ነው፤ ስለ ሆነም በዚህ ስፍራ የአካላትን ብዛት እንጂ አክብሮትን ለመግለጽ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳልተጠቀመበት በተከታይ የተጻፉት የብዛት መግለጫ የሆኑ ስሞች ተውላጠ ስሞና ግሶች የማያሻሙ ምስክሮች ናቸው፡፡
ለ.  መናፍቃኑ በክርክር ጊዜ ለመሸሽ የሚፈጥሩት ሌላው መደበቂያ መሰል ሐሳብ እንዲህ የሚል ነው፡- ይሆዋ ፍጥረታትን መፍጠሪያ እንዲሆነው ከፍጥረታት መፈጠር በፊት መሣሪያ የሆነ ፍጡር ፈጥሮ ነበርና “እኛ” እያለ ራሱን ለማስተዋወቅ የቻለው ይህንኑ የፍጥረት መጀመሪያ የሆነውን ፍጡር ከራሱ ጋር በመደመር የሁለትነት ብዛትን ለመግለጽ ነው ይላሉ። /6/ ዳሩ ግን ይሆዋ ፍጥረታትን በፈጠረ ጊዜ የረዳው ወይም እንደ መሣሪያ ያገለገለው፥ ሥልጣኑንና ክብሩን እየተጋራ “ኤሎሂም” /አማልክት/ በሆነው ይሆዋ አንዲት መለኮት ውስጥ ራሱን ማስገባት የቻለ ከእኔነቱ ውጪ ማንም አልነበረም፡፡ በብዙ ቊጥር በተነገረው ኤሎሂምነት /አማልክትነት/ የሚታወቀው አንዱ ይሆዋ ብቻ ያለ ረዳት ሁሉን እንደ ፈጠረ የእግዚአብሔር ቃል ያረጋግጣል (መዝ. 33፥6፤ 136፥1-9፤ ኢሳ. 44፥24፤ 45፥5፡8)፡፡
ሐ.  ይሆዋ ፍጥረትን በመፍጠር ሥራ እንዲረዳው አንድ መልአክ በመጀመሪያ ፈጥሮ ነበር፤ ቢሉም መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከሁሉ በፊት “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ያስተምራል፡፡ ከሰማይና ከምድር መፈጠር በፊት የተፈጠረ ሌላ ፍጥረት እንደሌለ ለአእምሮአችን የከለለው ግድግዳ ወይም ገደብ “መጀመሪያ” የሚለው ቃል ነው (ዘፍ. 1፥1)፡፡
መ. ኤሎሂም /አማልክት/ የሚለው የብዙ ቊጥር መግለጫ የሆነው ስምና ይሆዋ ራሱን ለመግለጽ የተጠቀመበት “እኛ” የሚለው ተውላጠ ስም መልአክን  ወይም ብዙ መላእክትን እንደሚጨምር ከአርዮሳውን በንግግር ብዙ ጊዜ ተስምቷል፡፡ መላእክትን የፈጠረ አምላክ ይሆዋ … የሚያደርገው የአርዮሳውያን ስብከት ትምህርተ አጋንንት እንደ ሆነ እንረዳለን (ዘዳ. 4፥39፤ ማቴ. 4፥8-11)፡፡
ሠ. ኤሎሄም /አማልክት/ በመጀመሪያ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ የሚለው ጥቅስ ይሆዋና መልአክን አዳምሮ እንዲገልጽ የታሰበ ቢሆን ኖሮ የአረፍተ ነገሩ ማሰሪያ አንቀጽ “ፈጠሩ” ማለትን ባስከተለ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በዚህ ጥቅስ “ኤሎሂም /አማልክት/” የሚለውን የብዙ ቁጥር መግለጫ የሆነውን ስም የአረፍተ ነገሩ ባለቤት አድርጎ ሲያቀርብ፥ በኤሎሂምንት /አማልክትነት/ መገለጽ የተገባቸው አካላት መኖራቸውን እያመለከተ መለኮታውያን የሆኑት አካላት የሥልጣን፣ የክብር፣ የኀይል፣ የጌትነት፣ … ተዋሕዶ /አንድነት/ እንዳላቸው ለማስገንዘብ የአረፍተ ነገሩን ማሰሪያ አንቀጽ እንደ አረፍተ ነገሩ ባለቤት ለብዙ ቊጥር የሚስማማ አላደረገም፡፡ ማለት “አማልክት … ፈጠሩ” ሳይል “አማልክት ፈጠረ” ብሏል፡፡ በኤሎሂም ብዛትን በፈጠረ አንድነትን አጣምሮ የሚሰብክ ትምህርተ ሃይማኖት ከመጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ መጽሐፍ፥ መጀመሪያ ምዕራፍና መጀመሪያ ቊጥር መቀበላችንን እንረዳለን፡፡ በዚህ በኩል ከመጡብን ከሓድያንና መናፍቃን ሊጠብቀን እግዚአብሔር ከጥንቱ እንዴት እንዳሰበልን በማጤን ኤሎሂም የሆነውን ይሆዋን ልናመሰግን ይገባል፡፡
ረ.  በዚሁ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ በየዕለቱ ለተፈጠሩት ፍጥረታት ፈጣሪያቸው “ኤሎሂም /አማልክት/” እንደ ሆነ ሲነገር የማሰሪያው አንቀጽ ነጠላ ቊጥር መሆኑ አልተዛባም (ዘፍ. 1፥1-25)፡፡

No comments:

Post a Comment