Sunday, January 15, 2012

በኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

    Read PDF
በጮራ ቊጥር 2 ላይ የቀረበ

/ካለፈው የቀጠለ/

በዚህ ርእስ የሚቀርበው ታሪክ ከጥንት ጀምሮ እየተለዋወጠ እስከ እኛ ዘመን የደረሰውን የሀገራችንን የዳር ድንበር ክልል፥ የመንግሥቷን ዐይነትና አወቃቀር በየዘመኑ በመንግሥቷ የታቀፉትን ልዩ ልዩ ነገዶች ስማቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ አምልኮታቸውን ወዘተርፈ በመጠኑም ቢሆን መያዝ በተገባው ነበር፡፡ ዳሩ ግን በአንድ በኵል ከርእሱና ከዐላማው ላለመውጣት፥ በሌላው በኩልም በሙያው ብዙ የደከሙትን ተመራማሪዎች ድርሻ ላለመሻማት ሲባል በርእሱና በዐላማው መወሰን የሚሻል ሆኗል፡፡

          ሊቀር የማይገባው ነጥብ ቢኖር “ኢትዮጵያ” ስለሚለው ስያሜ ዐጭር መግለጫ የማቅረቡ ጕዳይ እንደ ሆነ ይታመናል፡፡
ለኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ የሚያገለግሉ ምንጮች ናቸው በመባል በባለታሪኮች ከሞላ ጐደል የሚታመንባቸው፡-


1.       በሰባ /70/ ሊቃውንት ከዕብራይስጥ ወደ ጽርእ የተተረጐመው “ሰብትዋጀንት” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም
2.      ከ13ኛው መቶ ዓመት ጀምሮ በግእዝ የተጻፉ የነገሥት ታሪክ መጻሕፍት
3.      የገድልና የድርሳን መጻሕፍት
4.      በቀድሞ ዘመን በሀገሪቱ ውስጥ ባንዳንድ ቦታ በተፈለፈሉ ዋሻዎች ውስጥና በሐውልቶች ላይ የተገኙ ቅርጻ ቅርጾችና ጽሑፎች
5.      ኢትዮጵያን ከጐበኙ በኋላ ታሪኳን ከጻፉ የውጭ ሀገር ሰዎች የጉዞ ማስታወሻዎች
6.     በጥንታዊ መዲናዎች ከተማዎች መንደሮች አብያተ ክርስቲያን … ፍርስራሾች ሥር ከዓመታት በፊት ተቀብረው የነበሩና ተመራማሪዎች በቊፋሮ እየለቀሙ ያወጧቸውና የሚያወጧቸው ማስረጃዎች
7.      ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን በሙሉም ሆነ በከፊል ዋቢ በማድረግ የጐደለ የመሰላቸውንም በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ በመተላለፍ ሲነገር ከቈየው የሚያምኑበትን መርጦ በማከል ከሀገር ተወላጆች የተጻፉ የታሪክ መጻሕፍት ሲሆኑ አሁን ለተነሣንበት ርእስ ግን በተራ ቊጥር 1 ከተገለጸው ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጥቅሶችን በመውሰድ በእደ አእምሮ የሚያስጨብጡንን እውነታዎች በመጠኑ እንዳስሳለን፡፡



በእጃችን የሚገኙት የግእዝና አብዛኞቹ የዐማርኛ ቅዱሳት መጻሕፍት /መጽሐፍ ቅዱስ/ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ260-222 ዓመት ባለው ጊዜ መካከል በእስክንድርያ በ70 የአይሁድ ሊቃውንት ከዕብራይስጥ ወደ ጽርእ ከተመለሰው “ሰብትዋጀንት” በመባል ከሚታወቀው አብነታዊ መጽሐፍ ቅዱስ የተተረጐመ እንደ ሆነ ተረጋግጧል፡፡ ስለ ሆነም፡-

ሀ.  በዕብራይስጥ “ኵሽ” ተብሎ የተጻፈውን የካምን ልጅ ስም ተርጓሚዎች በጽርእ “ኢትዮጵስ” ብለውታል፤ ለምሳሌ፡- ዘፍ. 2፥13፤ ኢሳ. 18፥1፤ 45፥14፤ ኢዮ. 28፥19፡፡ በጽርእ “ኢትዮ” ማለት ጥቊር፥ ጠቋራ፥ ከሰልማ፥ “ጵያ” ማለት ፊት ማለት ነው፡፡ ተያይዞ ሲነበብም ፊተ ጠቋራ፥ ሻንቅላ እንደ ማለት ነው፡፡ ነገደ ኵሽ ከሰፈሩበት የመሬት አቀማመጥና የአየር ጠባይ የተነሣ ስለ ጠቈሩ የመልካቸውን ቀለም እንዲገልጽላቸው በመሻት እንደ ዕብራይስጡ ኵሽ ከማለት ይልቅ በጽርኡ ኢትዮጵያ ማለትን ተርጓሚዎቹ መርጠው ይሆናል (ኤር. 13፥23፤ ዘኍ. 12፥1)፡፡

ለ. ነገደ ኩሽ የሰፈሩበትን በሐሩር የተቃጠለውን በዕብራይስጡ የበረሓ ትርጕም ያለውን ቈላማ መሬት ተርጓሚዎቹ በጽርእ ኢትዮጵያ ብለውታል፡፡ ለኵሽ ልጆች መኖሪያቸው የሆነው በረሓ “ኢትዮጵያ” መባሉ በጥቊረታቸው ምክንያት ሆኗል በሚል አስተሳሰብ ተነሣሥተው ሊሆን ይችላል የሚል ግምታዊ አነጋገር አለ (መዝ. 72፥9፤ 74፥14)፡፡

ሐ. በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳንም ቢሆን አንዳንድ ጥቅሶች ኢትዮጵያ በሚል ቃል መጻፋቸው ተረጋግጧል (መዝ. 68፥31)፡፡

መ. በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ኩሽ ወይም የበረሓ ትርጕም ያለው ስም በጽርኡ ብሉይ ኪዳን ኢትዮጵያ ተብሎ መተርጐሙና ይኸው ቃል በዐረብኛው ትርጉም “ሱዳን” መባሉ ለጥቊረትና ለበረሓማነት መግለጫ ነው የሚለውን ሐሳብ ያጠናክራል የሚሉ አሉ፡፡

እንግዲህ ኵሽ /ኢትዮጵያና ሱዳን/ ከግብጽ ጋር ወሰነተኞች የነበሩበትና እርስ በርስም የተገዛዙበት ጊዜ እንደማይጠፋ በመጠቈም የዛሬዎቹ ኢትየጵያ፣ ሱዳን፣ ግብጽ እንደ አንድ የተጠቃለለ የመንግሥት ሀገር፥ ወይም በየራሳቸው በተለይም ይህን ስም ተጠርተውበት እንደ ነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፡፡ በሰብትዋጀንት ተርጓሚዎች አመለካከት ቀጥሎ የተገለጹት ሐሳቦች የተካተቱ ይመስላል፡፡

1.    ኵሽ /ኢትዮጵያ/ በግብጽ ቦታ ሲነገር፡-

2ነገ. 18፥19-25፤ ከ2ነገ. 19፥5-13፤ ኢሳ. 36፥4-10፤ 37፥8-13 ጋር ተገናዝቦ ይነበባል፡፡
2.   ኵሽ /ኢትዮጵያ/ በዛሬዪቱ ሱዳን ቦታ ሲነገር

ኤር. 46፥25፤ ናሆ. 3፥8፡9፤ ሐ.ሥ. 8፥27-39፤ ሕዝ. 29፥10፡፡

3.   ኵሽ /ኢትዮጵያ/ ምድረ በዳ ቈላ ሆኖ ሲነገር

ሀ. መዝ. 74፥14 የሌዋታንና /ዘንዶውን/ ራስ ቀጠቀጥህ፥ “ለምድረ በዳ ሕዝቦች” ምግብ አድርገህ ሰጠሃቸው ተብሎ በዕብራይስጥ የተነገረውን ሲተረጕሙ “ለኢትዮጵያውያን” ማለታቸው ነው፡፡
ለ. መዝ. 72፥8-9 “የምድረ በዳ አራዊት” በፊቱ ይገዛሉ፤ የሚለው “ሕዝበ ኢትዮጵያ” መባሉ መላው የአፍሪካን በረሓማ መሬት ያጠቃልላል የሚለውን አተረጓጐም በተጨማሪ ያጐልብተዋል፡፡

ሐ. የሳባ /ሼባ/ ንግሥት የእስራኤልን ንጉሥ ሰሎሞንን ዝና እንደ ሰማች ልትጐበኘው መሄዷ ተተርኳል (1ነገ. 10፥1፤ 2ዜና. 9፥1)፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ታሪኩን ጠቅሶ ሲያስተምር “የአዜብ ንግሥት” ብሏታል (ማቴ. 12፥42)፡፡













                            
“አዜብ” የተባለው በደቡብና በምዕራብ መካከል ያለውን አቅጣጫ ስለሚያመለክት፥ ተናጋሪው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለነበረበት ወይም ንግሥተ ሳባ ለጐበኘችው ለሰሎሞን ሀገር እንደ አዜብ የሚቈጠረው፥ ከግብጽና ከሊቢያ ጀምሮ ወደ ደቡብ፥ ከዐባይ ወንዝ እያካለለ የተዘረጋውን በረሓ ስለ ሆነ የላይኛውን አባባል ያጸድቀዋል፡፡

4.   ኵሽ /ኢትዮጵያ/ የሳባውያንን አገርና መንግሥት ያመለክታል

ከታሪከ ነገሥት አገላለጽና ከባለታሪኮች ትረካ እንደምንረዳው እስከ ዘመናችንም የደረሰውና የወረስነው ትውፊት በቀድሞ ዘመን ሳባውያን የያዟትና ከነገደ ኵሳ/ከኵሻውያን ጋር በመደባለቅ የኖሩባት መዲናቸው ሳባ-አክሱም የነበረው የአሁኗ ኢትዮጵያ በዚህ ስም ትጠራለች፡፡ ያላለቀ ክርክር ቢኖርም ሰሎሞንን የጐበኘችው ሴት ምናልባት እስከ ግብጽ ወሰን ድረስ የተዘረጋውን በረሓማውን አገር በሙሉ አጠቃልላ ትገዛ የነበረች ንግሥት ትሆን ይሆናል፡፡

5.   አጠቃላይ ስም

ኵሽ /ኢትዮጵያ/ ከዚህ በላይ ከ1 እስከ 4 የተዘረዘሩትን ብሔሮች፥ አቅጣጫዎች፥ ማለት የዛሬዎቹን ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብጽና ለኢየሩሳሌም በአዜብ አቅጣጫ ያለውን የአፍሪካ በረሓማ መሬት አጠቃሎ የሚገልጽ ስም ሆኖ አገልግሏል ማለቱ ከእውነት ያልራቀ አባባል ነው፡፡
በ2ዜና 14፥9-13 እና 16፥8 ኵሽያውያን /ኢትዮጵያን/ እና ሊብያውያን የተጠቃለሉበት ወደ ምድረ እስራኤል ዘምቶ የነበረው ወታደራዊ ኀይል በእግዚአብሔር ድል እንደ ተመታ ተተርኳል፡፡ የኢትዮ-ሊቢያ ጦር ወደ እስራኤል ምድር ሊዘምት የሚችለው ወይ በግብጽ መሪነት ወይም ግብጽን ድል በመምታት ከራሱ ጋር አዋሕዶ መሆን እንዳለበት አይካድም፡፡ ስለ ሆነም ጦሩ የተጠራው በኢትዮጵያ ስም ነው፡፡


ማጠቃለያ፥ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች በተባለው ትንቢታዊ ቃል መሠረት በዚህ አገር ወይም አቅጣጫ የምንገኘውን ሕዝበ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር እንደ ጐበኘን፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ለተቋቋመችው መንግሥቱ ወራሽነት እንደ መረጠንና እንደ ጠራን ዐውቀን የአምላካችንን ምሕረት ለማድነቅና ውለታውን እያሰብን ምስጋና ለማቅረብ ታሪኩ ይረዳናል ብለን እናስባለን (የሐዋ. 11፥17፡18)፡፡ በዚህ መንፈስ ካልሆነ በቀር ሰዎችን የሚለያየውን የትውልዶች ታሪክ ክርክር ለመጀመር እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል (ቲቶ 3፥9-10 1ጢሞ. 1፥3፡4)፡፡
ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment