(ሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር 39፥ በአለቃ ነቅዐ ጥበብ ዐምድ ውስጥ የቀረበው ትረካ ማጠንጠኛ የነበረው ሐሳብ “ያለ ወላዲተ አምላክ አማላጅነት ዓለም አይድንም” የሚለው ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ነበር። ከሰሞኑ ይህን ጥቅስ አስመልክቶ መምህር ያረጋል አበጋዝ፥ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያልኾነ ወፍዘራሽ ትምህርት መኾኑን ገልጦ ሲናገር ከማኅበራዊ ሚዲያ አድምጠናል። የስሕተት ትምህርቱ በርሱም ዘንድ ስሕተትነቱ በመገለጡ፥ እውነት ፍሬ ማፍራቱን እንድንረዳና ጌታን እንድናመሰግን ምክንያት ኾኖኗል። ከዛሬ 13 ዓመት በፊት የወጣውን ዘለግ ያለ ጽሑፍ እንድታነብቡት ጋብዘናል።)
ትረካ
በቅርቡ ወደ ርእሰ ሕይወት መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የጕዞ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ለብዙ ዓመታት በተከፈለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ከተለያዩ የስሕተት ትምህርቶችና ከመናፍስት አሠራሮች ነጻ የወጣና ምንም ያልተቀላቀለበት ንጹሕ ወንጌል የሚሰበክበት፣ ያልተቀያየጠ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት ደብር ነው፡፡ ደብሩን የሚያውቁት በዚያ ያሉ ወንድሞችንና እኅቶችን ለመጐብኘትና ከእነርሱ ጋር መንፈሳዊ ነገርን ለመከፋፈል÷ ዝናውን የሰሙት ደግሞ የተባለው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ የጕዞው እድምተኞች ሆነዋል፡፡
አለቃ ነቅዐ ጥበብና ከደቀ መዛሙርቶቻቸው ጥቂቶች÷ እንዲሁም ወደ ስፍራው ለመሄድ የተዘጋጁ ሌሎች ወገኖችም ማልደው በስፍራው ተገኝተዋል፡፡ ወደሚጓዙበት አውቶቡስ ከገቡ በኋላ ጕዞ ከመጀመሩ በፊት÷ ቀሲስ ፍሬ ጽድቅ ጕዟቸውን ለታመነው ፈጣሪ ለእግዚአብሔር በጸሎት ዐደራ ሰጡና ጕዞው ቀጠለ፡፡
ግማሽ ሰዓት ያህል እንደ ተጓዙ ቀደም ብሎ ያልተያዘ÷ ነገር ግን እዚያው የተፈጠረና አነጋጋሪ የነበረ አንድ ርእሰ ጕዳይ ተነሣ፡፡ ላነጋገረው ርእሰ ጕዳይ መነሻ የሆነው በአውቶቡሱ ውስጥ ፊት ለፊት÷ ሁሉም ሊያነበው በሚችልበት ቦታ ላይ የተለጠፉትና «ያለ ወላዲተ አምላክ አማላጅነት ዓለም አይድንም» እና «ያለ ቅድስት ድንግል ማርያም ክርስትና የለም» የሚሉት ምንጭ አልባ ጥቅሶች ናቸው፡፡
እርስ በርስ መነጋገሩና መከራከሩ ከፊት አካባቢ በተቀመጡት ምእመናን መካከል ተጀምሮ በአውቶቡሱ ውስጥ ወዳሉት ተጓዦች ሁሉ ተዛመተ፡፡ መኪናው ገበያ የቆመበት ስፍራ እንጂ አውቶቡስ አልመስል አለ፡፡ ከጕዞው አስተናባሪዎች አንዱ የሆነው ዲያቆን ላእከ ኢየሱስ ጫጫታውን ለማስቆም እያጨበጨበ÷ «እንደማመጥ ... እንደማመጥ ... እባካችሁ ... አንድ ጊዜ ጸጥታ .... ጸጥታ» ሲል ሁሉም ቀስ በቀስ ጸጥ እያለ መጣ፡፡ ... ከአውቶቡሱ የሞተር ድምፅ በቀር የሚሰማ አልነበረም፡፡ ዲያቆኑ ቀጠለ፡፡ «ምን ይሆን እንዲህ የምትከራከሩበትና የምትወያዩበት ጕዳይ?» ሲል ጠየቀ፡፡ ነገሩን የሰማው ቢሆንም÷ ውይይቱ መደማመጥ የሌለበት የግል ከሚሆን ይልቅ÷ የጋራ መወያያ ቢሆን ሁሉም ጠቃሚ ትምህርት ሊያገኝ ይችላል በሚል፡፡
ክርክሩን ካነሡትና ጥቅሱ ትክክል ነው ከሚሉት ወገን የሆነው÷ ወጣት እንዳሻው «ይህ ጥቅስ አሁን ምን ይወጣለታል? ያለ ጌታ እናት አማላጅነት ዓለም ሊድን እንዴት ይችላል? ያለ እርሷስ ክርስትና አለ ሊባል እንዴት ይችላል?» ሲል በንዴትና በቊጣ ተናገረ፡፡ «አዎን! ... ልክ ነው! ... ይህ ስሕተት ነው የምትሉ ካላችሁ እስኪ መልስ ስጡ! ... በሉአ!» አሉ እማሆይ ጸዳለ ማርያም፡፡ ሌሎች የዚህ ሐሳብ ደጋፊዎችም «እኮ በሉአ! ... እኮ እንስማችሁ!» አሉ እየተቀባበሉ፡፡
ዲያቆን ላእከ ኢየሱስ÷ «መልካም! ለሁሉም እየተደማመጥን እንወያይ፡፡ ውይይታችን እውነትን ለማወቅና በእውነት ዐርነት ለመውጣት እንጂ ለዐጕል ክርክር ብቻ ባይሆን መልካም ነው፡፡ ወይይቱ በሥርዐት እንዲካሄድ እኔ እመራለሁ፡፡ ሐሳብ ያላችሁ እጅ እያወጣችሁ ሐሳባችሁን ታቀርባላችሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ንግግር ባይኖር ጥሩ ነው፡፡ ተስማማን?» በማለት የጕዞ ላይ ውይይቱን መሥመር ለማስያዝ ሞከረ፡፡ ተጓዡም እሺታውን ከገለጸ በኋላ ውይይቱ ቀጠለ፡፡
«በቅድሚያ ጥቅሶቹን የለጠፋቸው እርሱ ሊሆን ስለሚችል እስኪ ለሾፌሩ ዕድል እንስጥ» አለ አወያዩ፡፡ «ድንቅ!» አሉ እማሆይ ከሾፌሩ ጥሩ ሐሳብ እንደሚሰሙ ተስፋ አድርገው፡፡ ብዙዎቹም «ጥሩ ነው! ... ጥሩ ነው!» አሉ፡፡ ሾፌሩም «አመሰግናለሁ! በቅድሚያ እንድታውቁልኝ የምፈልገው÷ ይህ መኪና የእኔ አይደለም፡፡ እዚህ መኪና ላይ ተቀጥሬ መሥራት ከጀመርሁም ጥቂት ጊዜ ነው፡፡ መኪናውን ስረከብ ጀምሮ ጥቅሶቹ ነበሩ፡፡ አልዋሻችሁም! ጥቅሶቹን እንዳየሁ ዛሬ በአንዳንዶቻችሁ ውስጥ ጥያቄ እንደ ተፈጠረ ሁሉ እኔም ደንገጥ ብያለሁ፡፡ እስከማውቀው ድረስ እንዲህ ያለ ትምህርትም ሆነ እምነት መኖሩን እስከዚያ ጊዜ ድረስ አላውቅም ነበር፡፡ ሆኖም የአውቶቡሱ ባለቤት ለእመቤታችን ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ ስለ ሆነና ከእግዚአብሔር በላይ ስለሚወዷት ጥቅሶቹን እንደ ለጠፏቸው በኋላ ላይ ተረድቻለሁ፡፡ የማርያም ናቸው በተባሉ ሥዕሎች ጋቢናውን የጸሎት ቤት እንዳስመሰሉትም መመልከት ትችላላችሁ፡፡» ሲል በመጨረሻው ንግግሩ አንዳንዶቹ እንደ መሣቅ አሉ፡፡ እማሆይ ጸዳለ ማርያም ግን ቈጣ ብለው ምን ያስገለፍጣችኋል? «ሥዕለ ማርያም መቀለጃ ናት?» ሲሉ÷ «እውነታቸውን ነው!» አለ ሌላው ቀበል አድርጎ፡፡
ዲያቆን ላእከ ኢየሱስ ወይይቱ ከመሥመር እንዳይወጣ÷ «መልካም! ሾፌሩ ጥቅሶቹን በተመለከተ ያለውን ሁላችሁም ሰምታችኋል፡፡» በማለት ወደ ዋናው የመወያያ ርእስ እንዲመለሱ ካደረገ በኋላ÷ ቀጣዩን የመናገር ዕድል ለመሪጌታ በእደ ማርያም ተሰጠ፡፡
እርሳቸውም÷ «እኔን የሚገርመኝ» አሉ፤ «እኔን የሚገርመኝ ሌላ ሳይሆን÷ በየዋህነት ልንቀበለው የሚገባው ይህ እምነታችን ለውይይት መቅረቡ ነው፡፡ ከተጠየቀ ግን መቼም መልስ መስጠት ግድ ነው፡፡ ኧ.. ብዙ ርቀን ሳንሄድ እዚህ ያለን አገልጋዮችም ምእመናንም ዘወትር ጸሎተ ኪዳን ሊደርስ ሲል አስቀድሞ በምናዜመው የኪዳን ሰላም ውስጥ ‘ብኪ ድኅነ ዓለም - ዓለም ባንቺ ዳነ’ የሚል ዘር እናገኛለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሷ ሥጋ ከእርሷ ተወልዶ ነውና ዓለምን ያዳነው÷ ዞሮ ዞሮ ዓለም የዳነውና የሚድነው በእርሷ አማካይነት እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ያለ እመቤታችን መዳንም ሆነ ክርስትና የለም! ቢባል እውነት እንጂ ሐሰት አይደለም» አሉ ፍርጥም ብለው፡፡
ቀጥሎ ሐሳብ ለመስጠት መምህር ጥዑመ ልሳን እጃቸውን አወጡ፡፡ ከአወያዩ ፈቃድ ሲያገኙም መናገር ቀጠሉ፡፡ «በቅድሚያ መሪጌታ ባቀረቡት አመለካከታቸው ላይ ሐሳብ ከመስጠቴ በፊት÷ የክርስትና ትምህርት የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መሆኑን አጽንዖት ሰጥቼ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ይህ የእኔ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሐሳብና የክርስትናም መርሕ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡» አሉና ቀጥሎ ለሚያቀርቡት ሐሳብ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ፡፡ አስከትለውም÷ «ወገኖቼ ስለ ክርስትና ትምህርትና እምነት ለመናገር መሠረት ማድረግ ያለብን መጽሐፍ ቅዱስን እንጂ ሌሎች መጻሕፍትን አይደለም፡፡ ሌሎች መጻሕፍትን መጥቀስ የምንችል ቢሆንም እንኳ÷ የምንጠቅሰው ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚስማማና የማይጣላ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ አሁን መሪጌታ በእደ ማርያም ያቀረቡት ሐሳብ በጥቅስ የተደገፈ ነው፡፡ ቁም ነገሩ ሐሳቡ በጥቅስ ተደግፏል የሚል ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ጥቅሱ ከየት ተጠቀሰ? በጥቅሱ ውስጥስ እውነት አለ ወይ? የሚሉት ነጥቦች ሊተኰርባቸው ይገባል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ከመጽሐፍ ቅዱስ እንጠቅሳለን፡፡ አጠቃቀሳችን ግን ትክክለኛ ላይሆን ይችላል፤ ቃሉን ለተነገረበት ዐላማ ሳይሆን እኛ እንዲደግፍልን ለምንፈልገው ሐሳብ ይሆናልና የምንጠቅሰው፡፡ በዚህ መሠረት መሪጌታ የጠቀሱትና በአንቺ ዓለም ድኗል የሚለው ቃል ትክክል አይደለም እላለሁ፡፡ ይህን የምለው በዋናነት ቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰ ባለመሆኑ ብቻ አይደለም፤ የጥቅሱ መልእክት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር ስለማይስማማና ስለሚጋጭም ነው፡፡ ዓለም የዳነው በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ‘ዓለም የዳነው በማርያም ነው’ የሚልም ሆነ ‘ያለ ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም’ የሚል ቀርቶ÷ ከዚህ ጋር የሚጠጋጋ አንድ ጥቅስ ግን ማቅረብ አይቻልም፡፡ ስለዚህ እኒህ በመኪናው ውስጥ የተለጠፉትም ጥቅሶች ሆኑ እርስዎ ማስረጃ ብለው የጠቀሱት ከክርስትና ትምህርት ውጪ ናቸው» አሉ፡፡ «በመጨረሻ ማንሣት የምፈልገው አንድ ነገር አለ» ሲሉ ሁሉም ምን ሊሉ ይሆን በሚል ጕጕት ይበልጥ ነቃ ብሎ ይሰማቸው ጀመር፡፡
እርሳቸውም ቀጠሉ «ጌታ ከእመቤታችን ከቅድስት ማርያም ሰው ሆኖ ተወልዷል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ለእርሷም ክብሯ የጌታ እናት መሆኗ ነው፡፡ የተወለደውና ያዳነን በእርሷ ሥጋ ነው በሚልና ከተጻፈው በማለፍ÷ የልጇን የአዳኝነት ሥራ ለእርሷ ማዛወር ግን ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ብቻ ሳይሆን ምክንያታዊም አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡- የአንዱ ጀግና ወይም ዝነኛ ሰው እናት ጀግና ወይም ዝነኛ ልጅ በመውለዷ ክብር ይሰጣታል፡፡ የክብሯ ምክንያትም የልጇ ጀግንነት ወይም ዝነኛነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ መነሻነት ጀግናው ወይም ዝነኛው እርሱ ሳይሆን እርሷ ናት ማለት ግን አይደለም፤ በእርሱ ጀግንነትና ዝና ከምትከበር በቀር የእርሱን ዝናና ክብር ለራሷ ልትወስድ አትችልምና፡፡
«ቅድስት ማርያምም የጌታ እናት በመሆኗና ለዚህ ታላቅ ዕድል በመመረጧ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይላታል፡፡ ብፅዕት የመባሏ ምክንያቱም ሌላ ሳይሆን እርሷው እንደ መሰከረችው እግዚአብሔር በእርሷ ታላቅ ሥራን ስለ ሠራ ነው (ሉቃ. 1÷49)፡፡ ይሁን እንጂ የኢየሱስ እናት ስለ ሆነች እንደ ኢየሱስ አዳኝ ናት፤ የክርስትናም መሠረት ናት ማለት ግን ምክንያታዊ አይደለም፡፡» በማለት ንግግራቸውን ገታ አደረጉና ቀጠሉ፡፡ «ኧ ... በነገራችን ላይ ‹ብፅዕት› የሚለውን ቃል ብዙዎች ለድንግል ማርያም ብቻ እንደ ተነገረ ያህል ይቈጥሩታል፡፡ ነገር ግን ይህ ‹የተባረከ ደስተኛ› የሚል ፍቺ ያለውን ብፁዕ የሚለውን ቃል÷ ለእርሷ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የእግዚአብሔር አገልጋዮች ተቀጽሎ እናነባለን፡፡ እመቤታችን ራሷ ‹እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል› አለች (ሉቃ. 1÷48)፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብ ደግሞ÷ ‹እነሆ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን› ሲል ቃሉ በልዩ ልዩ ሁኔታ እግዚአብሔርን ላገለገሉ ቅዱሳን ሁሉ እንደሚቀጸል ያስረዳናል» አሉና ሐሳባቸውን ቋጩ፡፡
በዚህ ጊዜ ብዙ እጆች ወደ ላይ ተነሡ፡፡ ሆኖም ዕድሉ ለባሕታዊ ክንፈ ዑራኤል ተሰጠ፡፡ እርሳቸውም ጕረሮአቸውን በእህታ ጠራረጉና «መቼም በ8ኛው ሺህ ላይ ስለ ሆንን ትንቢቱ ሊፈጸም የግድ ነውና የእመቤታችንን ክብር ለመቀነስ ጥረት ቢደረግ ድንቅ አይደለም፡፡ እኛ እንዲህ ስላልን እርሷ መትሕተ ፈጣሪ (ከፈጣሪ በታች) እና መልዕልተ ፍጡራን (ከፍጡራን በላይ) መሆኗ አይቀርም፡፡ ይብላኝ ከክብሯ ዝቅ ሊያደርጋት ለሚያስብ» አሉ ዐይናቸውን በመምህር ጥዑመ ልሳን ላይ እንደ ተከሉ፡፡
አስከትለውም አባ ጽጌ ድንግል በደረሱላትና ማሕሌተ ጽጌ ላይ÷ «በከመ ይቤ መጽሐፍ ማእከለ ፈጣሪ ወፍጡራን÷ ለዕረፍት ዘኮንኪ ትእምርተ ኪዳን÷ ሰንበተ ሰንበታት ማርያም ዕለተ ብርሃን÷ ብኪ ይትፌሥሑ ዘገነተ ጽጌ ጻድቃን ወብኪ ይወፅኡ ኃጥኣን እምደይን» የሚለውን ጠቀሱ፡፡ ከዚያ «ይህ እርሷ አዳኝ÷ የክርስትናም መሠረት መሆኗን የሚያመለክት አይደለም?» ሲሉ ጠየቁ፡፡
«ምን
ማለት እንደ ሆነ ትርጕሙን ይንገሩን» አሉ አንዳንዶች፡፡
«ደኅና!»
አሉና ወደ መተርጐም ገቡ፡፡ «‘መጽሐፍ እንዳለ በፈጣሪና በፍጡራን መካከል ለዕረፍት የምልክት ኪዳን የሆንሽ የሰንበታት ሰንበት
ማርያም ሆይ! አንቺ የብርሃን ዕለት ነሽ፡፡ አበባ በሞላበት ገነት ውስጥ ያሉ ጻድቃን በአንቺ ደስ ይላቸዋል፡፡ በአንቺም
ኃጥኣን ከሥቃይ ስፍራ (ከሲኦል) ይወጣሉ’ ማለት ነው፡፡» በማለት ማብራራት ጀመሩ፡፡ «ያለ ምንም ማብራሪያ ትርጕሙ ብቻ እንኳ
በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ሊተኰርበት የሚገባው ‘መጽሐፍ እንደሚል’ የሚለው ሐረግ ነው፡፡ አባ ጽጌ ድንግል ይህን
ከልባቸው አንቅተው ሳይሆን መጻሕፍትን ምስክር ጠርተውና በመንፈስ ተቃኝተው የተናገሩት ነውና ሐሰት ነው ሊባል አይችልም፡፡
ስለዚህ ያለ እርሷ ዓለም እንደማይድንና በፈጣሪና በፍጡራን መካከል ያለችውም አማላጅ እርሷ እንደ ሆነች ሁላችሁም ዕወቁ፡፡»
በማለት ንግግራቸውን ጨረሱ፡፡
በዚህ ዐይነት አንዱ ለሌላው መልስ ይሆናል ያለውን እየሰጠ÷ ከሁለት ሰዓት በላይ ከተጓዙ በኋላ÷ ዲያቆን ላእከ ኢየሱስ ወደ ሾፌሩ ጠጋ አለና እጁን ወደ ቀኝ አቅጣጫ እየጠቈመ «እዚያ ዋርካ ጋ ስንደርስ ጥቂት ዕረፍት ብናደርግስ» ሲል ጠየቀው፡፡ ሾፌሩም ሲደርስ መኪናውን አቆመና ተጓዡ ሁሉ ወርዶ በየአቅጣጫው ተበታተነና ጥቂት ተናፍሶ ወደ ዋርካው ሥር እንዲሰበሰብ በአስተናባሪዎቹ ተጠራ፡፡ ቅርንፎቹን በሰፊው በዘረጋው ወርካ ሥር በሚገኘው ትልቅ ድንጋይ ላይ አለቃ ነቅዐ ጥበብ ተቀምጠዋል፡፡ በአውቶቡሱ ውስጥ እርሳቸው አድማጭ እንጂ ተናጋሪ ስላልነበሩ÷ አሁን ተራው የእርሳቸው መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነበርና ሊሰሟቸው÷ ዙሪያውን በተኮለኮሉት ድንጋዮችና በለምለሙ ሣሩ ላይ ጭምር ተቀመጡ፡፡
አለቃም «እስኪ እግዚአብሔር በመንገዳችን ሁሉ ስለ ጠበቀን እንወድሰው! ወደ እውነት ሁሉ እንዲመራንም እንጸለይ» ብለው ብድግ ሲሉ ሁሉም ተነሣ፡፡ አለቃ ቀጠሉ «ሁሉን ለራስህ ክብር ያደረግህ÷ እኛንም ለራስህ ክብርና መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ዳግመኛ የፈጠርኸን÷ የአባቶቻችን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ሆይ እናመሰግንሃለን፡፡ ሁላችንንም በመንገዳችን ከማንኛውም ክፉ ነገር ስለ ጠብቀኸንና እዚህ ስላደረስኸን በኢየሱስ ክርስቶስ በታዳጊያችን ስም ክብርንና ውዳሴን እናቀርብልሃለን፡፡ ጌታችን ሆይ! በመንገድ ላይ ሳለን ስንወያይበት የነበረውን ጕዳይ አንተ አድምጠሃል፡፡ ብርሃናዊ ወንጌልህ ካላበራለት በስተቀር ሰው እውነትህን ሊያስተውለው÷ አንተንም ሊያውቅህ አይችልም፡፡ ከአንተ ዘንድ እንደ ሆነ በመቊጠር በቅዱሳን ስም ራሳቸውን የሰየሙ መናፍስትን ከማምለክና ለእነርሱ ከመገዛት ነጻ አይወጣም፡፡ ስለዚህ ጌታችን ሆይ! አሁን በተጀመረው ውይይት ላይ ጥቂት ስንነጋር አንተ ከእኛ ጋር ሆነህ በሕያውና በሚሠራው ቃልህ የሁላችንንም ልብ እንድትነካ÷ የሁላችንም ዐይኖች እንዲከፈቱ እንለምንሃለን፡፡ ‘አንተን ያውቁ ዘንድ÷ የላክኸውንም ልጅህን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት’ ብሎ ውድ ልጅህ በሊቀ ካህንነቱ ባቀረበው ጸሎት ውስጥ እንደ ተናገረ÷ ማለቂያ ከሌለውና የአሮጊቶችን ተረት ከመሰለው ክርክር አውጥተህ÷ የዘላለምን ሕይወት ወደምናገኝበት የመዳን ዕውቀት እንድታፈልሰን እንለምንሃለን፡፡ በአንድ ልጅህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ያለ ክብር ጽንዕ ለአንተ ይገባል፤ ከእርሱ ጋር ማሕየዊ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን» ሲሉ ሁሉም «አሜን!» አለ፡፡$
ሁሉም ሰው ተቀመጠና አለቃ የሚናገሩትን ለመስማት ጆሮውን ወደ ንግግራቸው አዘነበለ፡፡ «ወገኖቼ ስሙ!» አሉ አለቃ፡፡ «እስካሁን በሁለት ጎራ አሰልፈው ሲያሟግቷችሁ ከነበሩት ጥቅሶች አንዱን «ያለ ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም» የሚለውን ጥቅስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ታክሲ የጀርባ መስተዋት ላይ ተለጥፎ ሳነብ ውስጤን ስቅጥጥ ነው ያደረገኝ፡፡ መቼም እንደ እኔ ያለ ስሜት የተሰማችሁ በመካከላችን ትኖራላችሁ ብዬ አምናለሁ» አሉና በዙሪያቸው ከብቦ የተቀመጠውን ተጓዥ ከዳር እስከ ዳር አንድ ጊዜ በዐይናቸው ገረፍ አደረጉ፡፡
አንዳንዶች «ልክ ነው፤ እኔንም እንደዚህ ያለ ስሜት ነው የተሰማኝ» በሚል ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡ አንዳንዶቹ ግን ጥቅሱ የፈጠረባቸው አንዳች ስሜት እንደሌለ ሁሉ ምንም ዐይነት ምላሽ በገጽታቸው ላይ አላሳዩም፡፡
«ይህ ስሜት ለምን እንደ ተሰማኝ ታውቃላችሁ? በጥቅሱ እንደ ተላለፈው ያለ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለማይገኝ ብቻ አይደለም ያዘንሁት፤ በእናት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስኖር ከልጅነት እስከ ዕውቀት ባሳለፍሁት ዘመን ሁሉ ሰምቼው የማላውቀው እንግዳ ነገር ስለ ሆነብኝም ጭምር ነው፡፡ በሌላም በኩል ስለ እኔ የሞተውን የጌታዬን አዳኝነት የሚጋርድብኝና ሌላ አዳኝ እነሆ! የሚለኝ መስሎ ስለ ተሰማኝም ውስጤ በጽኑ ነው የተቃወመው፡፡ በዚህ ጕዞ ላይ ጕዳዩ መነሣቱና መወያየታችን ደግሞ የማይገኝ መልካም ዕድል ሆኖ ተሰምቶኛልና አምላኬን አመሰግናለሁ፡፡»
አለቃ ቀጠሉ÷ «አሁን ባለን ዐጭር ጊዜ ስለ መጀመሪያውና ‘ያለ ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም’ ስለ ተባለው አነጋገር ሦስት ነጥቦችን ብቻ ነው የማነሣው፡፡»
«1ኛ. ጥቅሱ ከየት ተገኘ?
«መቼም
ሰው የፈለገውን አመለካከት የማራመድ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ክርስትናን እከተላለሁ የሚል ግን እንዲህ ሊል ከቶ አይችልም፡፡
የእኔ ሙግት ሰው እንደዚህ ብሎ ለምን ያምናል ሳይሆን÷ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውና የተደመደመው ክርስትና እንደህ
አያስተምርም ነው፡፡» በማለት ዐላማቸው የሰውን እምነትና አመለካከት መቃወም ሳይሆን የክርስትናን ትምህርት ከስሕተት ትምህርቶች
መከላከል መሆኑን አስጨበጡ፡፡
«መልካም»
አሉና ጥቂት ፋታ ከወሰዱ በኋላ «ለመሆኑ ይህ ጥቅስ ከየትኛው መጽሐፍ ይሆን የተጠቀሰው? መቼም ከጥሩው ምንጭ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተቀዳ
ነው የሚል ሰው እንደማይመጣ ርግጠኛ ነኝ፡፡ የጥንት አበውም እንዲህ የሚል ቃል ከአፋቸው አልወጣም፡፡» አሉ የመጀመሪያውን
ነጥብ ይበልጥ ግልጽ በማድረግ፡፡ ቀጠል አደረጉና «ርግጥ ቃል በቃል እንደዚህ ባይባልም÷ ቅድም መሪጌታ በእደ ማርያም እንደ ጠቀሷቸው
ዐይነት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሐሰተኛ መልእክቶች÷ የእርስዋ ባልሆኑና በጌታዬ እናት በቅድስት ማርያም ስም በተደረሱ አዋልድ
መጻሕፍት ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በጥቅሱ እንደ ተገለጸው ያለ የእምነት ዐቋምም ሆነ ትምህርት እናት ቤተ
ክርስቲያን እንደሌላት ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ጥቅሱ እገሌ ተናገረው ለማለት የማያስደፍር ምንጭ አልባ ነው፡፡
«አንድ አረፍተ ነገር ለጥቅስነት የሚበቃውና ተጠቃሽ ንግግር የሚሆነው÷ ቢያንስ በእውነታ ላይ ተመሥርቶና በውብ ቋንቋ ተከሽኖ ስሜትን የሚነካ፣ የማይረሳና ቁም ነገር ያለው ብሂል ሲሆን ነው፡፡ ይህን መመዘኛ አድርገን ብንወስድ÷ መወያያችን የሆነው ጥቅስ ስሜታቸውን የሚነካ አንዳንድ ሰዎችን አያጣም ይሆናል፡፡ ቢያንስ ግን በእውነታ ላይ ስላልተመሠረተ ተራ አረፍተ ነገር ከመሆን አያልፍም፡፡
«2ኛ. ጥቅሱ እንዴት ተሠራጨ?
«ካሁን
ቀደም ያልነበረውና በሊቃውንቱ ቀርቶ በምእመናን ዘንድ እንኳ የማይታወቀው ይህ ትምህርት እንዲህ ሊሠራጭ የቻለው እንዴት ነው?
ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡» አሉና እንደ መተከዝ ብለው ጥቂት ዝም አሉ፡፡ «በእኔ ግምት በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ስሕተት
የሆነው ይህ እንግዳ ትምህርት በዋናነት እየተነዛ ያለው መኪና ላይ በሚለጠፍ የማስታወቂያ ሥራ ነው፡፡ እነዚህን ሁለቱን ጥቅሶች
ብቻ አነሣን እንጂ እየተጻፈ የሚለጠፈው እኮ ብዙ ነው፡፡ ትምህርቱን እየነዙት ያሉት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያልዋሉና
ስለ ሃይማኖት ቢጠየቁ ሊመልሱ የማይችሉ ባዶ ቀናተኞችና ጽንፈኞች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
«እነርሱ ምን ያድርጉ! የወንጌልን እውነት ለመናገርና እምነትን ከስሕተት ለመጠበቅ የሊቃውንቶቻችንና የመሪዎቻችን አፍ ሲሸበብና ዝምታን ሲመርጥ እነርሱ ያለ ከልካይ እንዳሻቸው ፈነጩበት፡፡ መሪዎች ተመሪ÷ ተመሪዎች ደግሞ መሪ የሚሆኑበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነውና እናት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለውን ሥርዐተ አልበኛነት መሥመር ልታስይዝ ይገባል፡፡
«ይህን የስሕተት ትምህርት የወለደው ጽንፈኛ አመካከት ነው፡፡ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት ዓለም አይድንም የሚለውን የመዳን ትምህርት ለማስተባበል ጠላት ዲያብሎስ በንጹሑ የክርስትና ትምህርት ውስጥ የዘራው እንክርዳድ እንደ ሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ የሚገርመው ኢየሱስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው የሚለውን ትምህርት ለመቃወም ሁሉም የሚሽቀዳደመውን ያህል÷ ያለ ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም የሚለው ትምህርት ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት መሆኑን እያወቁ÷ መቃወም ቀርቶ አስተያየት እንኳ የሚሰጡበት መጥፋታቸው ያስገርማል፤ እርሱን መንካት ያስወግዛላ!! ዛሬ የሚያስወግዘው እኮ እውነትን መናገር ብቻ አይደለም፡፡ ውሸትንም መንቀፍ ያስወግዛል፡፡ ይህም የስሕተት ትምህርቶች እንደ ልብ የሚሠራጩበትን ሰፊ በር ሲከፍት÷ እውነት የሚነገርበትን ዕድል ደግሞ ጠባብ አድርጎታል፡፡
«3ኛ. ጥቅሱ ተቃውሞ ለምን ገጠመው?
«ጥቅሱ
ተቃውሞ የገጠመው በጭፍን ጥላቻ÷ ወይም አንዳንዶች ቀድሞ ያስወሩት እንደ ነበረው ‘ፀረ ማርያም’ ዐቋም በማራመድ አይደለም፡፡
ማንም ክርስቲያን ነኝ የሚል የጌታን እናት ሊቃወም አይችልም፡፡ ነገር ግን በጌታ እናት በቅድስት ማርያም ስም የተደረሱና ኢመጽሐፍ
ቅዱሳዊ ይዘት ያላቸው አመለካከቶች እርሷን አይወክሉም፤ ወደ አምልኮ ባዕድም ያሸጋግራሉ የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዐቋም ብዙዎች
እርሷን እንደ መቃወም አድርገው ቈጠሩት፡፡ እርሷን መቃወም ማለትስ በጥቅሱ እንደ ተገለጸው ያልሆነችውን ሆናለች÷ ያላደረገችውን
አድርጋለች ብሎ በፈጠራ ድርሰት የእርሷን መልካም ስም ማጥፋት ነው፡፡
«‘ያለ ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም’ የሚለው አነጋገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አለውን?» ሲሉ ጠየቁ፡፡ የማንንም ምላሽ ሳይጠብቁ «በፍጹም የለውም! እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተቃውሞ የሚነሣበት ኑፋቄ ነው» አሉ፡፡ ቀጠሉና «ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ መዳን የሚገኘው በማን ነው ይላል? ይህን ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማና በማያጠራጥር መንገድ÷ መዳን የሚገኘው ድንግል ማርያም በወለደችውና የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንደ ሆነ ይናገራል፡፡ ጥቂት ማስረጃዎችን ከቃሉ እንጥቀስ፡፡ ጌታ ስለ አዳኝነቱ ከተናገራቸው መካከል ጥቂቶቹ እነሆ÷
«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና፡፡ ... በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል፡፡ ... በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም፡፡» (ዮሐ. 3÷16፡18፡36)፡፡
«በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል÷ ይገባል ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል» (ዮሐ. 10÷9)፡፡
«ኢየሱስም፡- እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡» አለ (ዮሐ. 14÷6)፡፡
«ሐዋርያቱም ቢሆኑ ከእርሱ በቀር ሌላ የመዳኛ መንገድ እንደሌለ አስተምረዋል፡፡ በግብረ ሐዋርያት ከተጻፈው እንጀምር፡፡» አሉና በሐዋርያት ሥራ 4÷12 ላይ የተጻፈውን ቃል አነበቡ፡፡ «መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና»
«ሐዋርያው ጳውሎስም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው አንድ ብቻ÷ እርሱም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ አስተምሯል (1ጢሞ. 2÷5-6)፡፡ ልብ በሉ! መካከለኛው አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሌላ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እያለ ነው ሐዋርያው፡፡»
«እስኪ ፍረዱ! መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ እያለ ሌላ የመዳኛ መንገድ አለ ብሎ መስበክ÷ በመጽሐፍ ቅዱስ እመራለሁ÷ ክርስቲያን ነኝ ከሚል ወገን ይጠበቃልን? እኒህ ወገኖች እንዲህ በሚያደርጉ ላይ ሐዋርያዊ ውግዘት እንደ ተላለፈ ልብ አላሉ ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ እኛ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየውን ወንጌል የሚሰብክላችሁ ማንም ቢኖር የተረገመ ይሁን ብሏል፡፡ እኛም ራሳችን በመጀመሪያ የሰበክንላችሁን ወንጌል ለውጠን ቀድሞ የሰበክነው ስሕተት ነውና እርሱን ትታችሁ አሁን የምንሰብክላችሁን ሌላ ወንጌል ተቀበሉ ብንላችሁ÷ ወይም ከሰማይ የወረደ መልአክ ከተሰበከላችሁ ወንጌል ውጪ የሆነ ሌላ ወንጌል ልስበክላችሁ ቢል የተረገመ ይሁን ነው የሚለው፡፡ ከላይ እንደ ተገለጸው ሐዋርያው የሰበከው ወንጌል ‘መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ይገኛል’ የሚለው ነው፡፡
«ሌላው አስደንጋጭ መፈክርም ካሁን ቀደም ተሰምቶ አይታወቅም፡፡» አሉና በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ «እንዴ ሰዎቹ ምን እያሉ ነው? እውን እንዲህ ብሎ በመጀመሪያ የተናገረው ሰው ክርስቲያን ነው? ወይስ የበግ ለምድ የለበሰ ነጣቂ ተኵላ?» አሉ የሐዘን ቃና ባለው ድምፅ፡፡ «ስሙ እንደሚመሰክረው ክርስትና በክርስቶስ የተመሠረተና የተደመደመ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ክርስትና ከክርስቶስ በቀር ሌላ መሠረት የለውም፡፡ ልብ በሉ! የክርስትናን ሕይወት እንድትኖር የተጠራችውና የተመረጠችው ቤተ ክርስቲያን (ማኅበረ ምእመናን) የተመሠረተችው ‘አንተ ክርስቶስ÷ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ’ በሚለው የማይለወጥና የማይናወጥ የእምነት ዐለት ላይ ነው እንጂ÷ በሌላ ፍጡር ማንነትና ስም ላይ አይደለም (ማቴ 16÷18)፡፡ ከዚህ ውጪ ‘ያለ ቅድስት ድንግል ማርያም ክርስትና የለም’ የሚል ሌላ መሠረት አለ ባይ ቢመጣ÷ አንድ ጊዜ ለዘላለም የተመሠረተውን መሠረት ለማፍረስ የተነሣ ሐሳዊ ነውና አንቀበለውም፡፡
«ስለ መሠረቱ መጽሐፍ ምን አለ? ብትሉ÷ ‘ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና÷ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው’ ይላል (1ቆሮ. 3÷11)፡፡ የክርስትናን ሕይወት መኖርና ፍሬው የሆነውን መልካም ሥራን መሥራት የሚቻለው በዚህ መሠረት ላይ የተመሠረቱ እንደ ሆነ ብቻ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን ስለ መሠረቱ እውነተኛነት ምንም ሊጠራጠር አይገባውም፡፡ በዚህ መሠረት ላይ ስለሚያንጸው በጎ ምግባር ነው መጠንቀቅ ያለበት፡፡
«በአጠቃላይ ክርስትና አለ ወይም የለም የሚባለው በሌላ መለኪያ ሳይሆን÷ በክርስቶስና በትምህርቱ ጸንቶ በመኖርና ባለመኖር ነው፡፡ ክርስቶስ ማእከል የሆነበትና ትምህርቱ የሚታመንበት እርሱ ክርስትና ነው፡፡ ክርስቶስ የሌለበት ወይም ስሙ ለይስሙላ ብቻ እየተጠራ የአዳኝነቱ ስፍራ ለሌሎች የተሰጠበትና ትምህርቱም የተሸቃቀጠበት ከሆነ ግን÷ ሌላ ማኅበር እንጂ እርሱ ክርስትና ሊባል ሊሆንም አይችልም፡፡ ስለዚህ ያለ ክርስቶስ ክርስትና የለም ነው መባል ያለበት፡፡
«እኛም ጠላት ያስነገራቸውን የስሕተት ዐዋጆች÷ በተሰጠን የልጅነት መብት ገልብጠን የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን እናውጃለን፡፡ ያለ ክርስቶስ ቤዛነት ዓለም አይድንም!!! ያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስትና የለም!!!» ሲሉ÷ ብዙዎች የተገለበጠውን ዐዋጅ ደግመው ዐወጁ፡፡ ስፍራው በእልልታና በጭብጨባ ተናወጠ፡፡
አለቃ በሰጡት አስተያየት ብዙዎቹ ልባቸው ተነክቷል፡፡ ከመሪጌታ በእደ ማርያም ዐይኖች ግን እንባ መንታ መንታ እየሆነ ይፈስ ነበር፡፡ እስከ ዛሬ እውነት ብለው የያዙት ሁሉ ውሸት ሆኖ ቢያገኙት እግዚአብሔርን ሲያሳዝኑት ሕዝቡንም ሲያሳስቱት እንደ ኖሩ ተሰምቷቸዋል፡፡ ካቀረቀሩበት ቀና ሲሉ ከአለቃ ጋር ዐይን ለዐይን ግጥም አሉ፡፡ በመጨረሻ አለቃ ቀሪውን መንገድ ኖላዊ ትጉሕ (ትጉ እረኛ) ለሆነው አምላክ በጸሎት አሳልፈው በመስጠት ጕዞው ቀጠለ፡፡
No comments:
Post a Comment