Thursday, March 12, 2020


“ወንሕነሰ  ንሰብክ  ክርስቶስሃ  ዘተሰቅለ”
“እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (1ቆሮ. 1÷23)

የስብከተ ወንጌል ሥራ ሲታሰብ “መሰበክ ያለበት ማነው?” የሚለው ጥያቄ ሊመለስ የሚገባው ወሳኝ ጥያቄ ነው። በየሃይማኖቱ የሚሰበኩ ልዩ ልዩ አማልክትና አዳኞች ይኖራሉ። በክርስትና የሚሰበከው አዳኝ ግን አንድ ብቻ፣ እርሱም ሰው የኾነውና የተሰቀለው አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከእርሱ በቀር የሚሰበክ ሌላ አዳኝ የለም። ከእርሱ በቀር ሌሎችን “አዳኞች” አድርጎ የሚሰብክ ሰማያዊ መልአክም ኾነ ምድራዊ ሰው ቢኖር፣ ያ ልዩ ወንጌል ነውና እርሱ በሐዋርያት ቃል ውጉዝ ነው (ገላ. 1፥6-9)። 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ  እንዳይኾን ወንጌልን  እሰብክ ዘንድ ልኮኛል፤ የምሰብከውም በቃል ጥበብ ወይም “በሰዎች የንግግር ጥበብ” (ዐመት) አይደለም ይላል (1ቆሮ. 1፥17)። ይህም ወንጌሉ ከመስቀሉ ሥራ ጋር በጥብቅ የተቈራኘ መኾኑን ያስረዳል። የምንሰብከውም ሌላውን ሳይኾን “የተሰቀለውን” ክርስቶስን ነው። የመስቀሉ ቃል ወይም “ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ” የሚለው ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ቢኾንም፣ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነውና።

ከጥንት እስከ ዛሬ ለዚህ ወንጌል ሰዎች የሚሰጡት ምላሽም ኾነ አስተያየት የተለያየ ነው። የሰዎች ሐሳብና ፍላጎት ቢለያይም የወንጌሉ መልእክት ግን አይለወጥም። ሰዎች መስማት የሚፈልጉትን ሳይኾን ለሰዎች የሚያስፈልገውን እግዚአብሔር ያዘጋጀውን መድኀኒት እርሱንም የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን።

አይሁድ የተነገረውን ትንቢት የተቈጠረውን ሱባዔ እያወቁ፣ ዘመኑ ሲፈጸም ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በመካከላቸው እየተመላለሰ በቋንቋቸው ቢነግራቸውም እንኳ፣ በእርሱ ከማመን ይልቅ ሌላ ምልክት ይለምናሉ። ሰውን ለማዳን ያለፈባቸውን፦ ተራበ፤ ተጠማ፤ ደከመ፤ ተከዘ፤ ታመመ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ ተነሣ፤ ዐረገ፤ በአብ ቀኝ ተቀመጠ፤ ዳግመኛ ተመልሶ ይመጣል እየተባለ የተነገረውንና ለመዳናቸው የተከፈለላቸውን ካሳ ኹሉ አያምኑበትም።

እግዚአብሔር የአገልጋዮቹን (የባሪያዎቹን) ቃል ለማጽናትና ጸሎታቸውን ለመስማት፣ አእምሮኣቸው (ልቡናቸው) በሰይጣን የጨለመባቸውንና የታወረውን በወንጌል ብርሃን ለመግለጥ፣ ሥጋንም ነፍስንም ለመፈወስ በመንፈስ ኀይል በድንቅና በተኣምራት ያደረገውን መልካም ሥራ በመጥቀስ (በማስታወስ) አይሁድ አምላክነቱ በቂ ወይም ከበቂ  በላይ  መኾኑን  እያወቁ፣ እንደ ገና እንደ ሙሴ ባሕር  ከፍለህ፣ ጠላት ገድለህ፣ ደመና ጋርደህ፣ መና አውርደህ፣ የእሳት ዐምድ አቁመህ፤ እንደ ኢያሱም ፀሓይ አቁመህ፣ በረድ አዝንመህ፤ እንደ ጌዴዮንም ፀምር ዘርግተህ፣ ጠል አውርደህ፤ እንደ ኤልያስ እሳት አውርደህ፣ ዝናም አቁመህ ምልክት አሳየን የሚሉ ይመስሉ ነበር። እርሱ ግን ለእንደዚህ ዐይነቱ ትውልድ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር አይሰጠውም ሲል እቅጩን ነግሯቸዋል (ማቴ. 12፥39፤ 16፥4)።

ግሪኮችም (ጽርዓውያን) እግዚአብሔርን ሳያውቁ ወይም እርሱን የማወቂያ ፍለጋ (መንገድ) ሳይኾን የብቃታቸው ውጤት አድርገው፣ ሙፃአ ነፋሳትን፣ ምሕዋረ ከዋክብትን፣ ሚጠተ ብርሃናትን፣ አየረ አየራትን (ሰማየ ሰማያትን) ዑደተ መሬትን ወዘተ. እናውቃለን እንደሚሉትና ምርምር እንደሚያደርጉት እንደ ዘመናችን ሳይንቲስቶች ጥበብን ይሻሉ። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጥበብ የተነሣ እግዚአብሔርን በጥበባቸው አላወቁትም። በመኾኑም በጥበብ ሳይኾን ‘ኢየሱስ ስለ ኀጢአታችን ተሰቅሎ ሞተ፣ እኛን ስለ ማጽደቅም ከሙታን ተለይቶ ተነሣ’ በሚለው የስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ኾኗል። የእግዚአብሔር ጥበብ የተባለውም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እኛ ግን ምልክትን ለሚለምኑትም ጥበብን ለሚሹትም፣ እንደ ሞኝነት የተቈጠረውን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን።
 
ከተሰቀለው የሚበልጥ ድንቅ፣ ስለ ኀጢአታችንም ከሞተው የሚልቅ ምልክት የለም። ከእርሱነቱ ሌላ ምልክትን ለሚሹ “ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ኾናቸው፥ እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይኾናል” ብሎ ራሱ ጌታችን ተናግሯል (ሉቃ. 11፥30)። በሰዎች ሕይወት ውስጥ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከተደረገው ምልክት የሚበልጥ ድንቅና ተኣምር ከቶ የለም። በዚህ ሳይረኩ ወይም ይህን ዐልፈው ሌሎች ድንቆችና ተኣምራትን ፍለጋ መንከራተት ከታላቁ የድንቅና ምልክት ማማ ላይ መውረድ ይኾናል።

ብዙዎች ይህን ባለማስተዋል ከጥንት ጀምሮ በዚህ ድንቅ ምልክት ሲያፌዙና ሲሣለቁ ማየት ዐዲስ ነገር አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና አገልግሎቱ የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው ሰማዕያኑ የግሪክ ሰዎች “ዐዲሶቹን አማልክት የሚያወራ ይመስላል አሉ። ... ይልቁንም የሙታንን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኩሌቶቹ አፌዙበት፤ እኩሌቶቹ ግን ስለዚህ ነገር ኹለተኛ እንሰማሃለን አሉት፤ ... አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ (ሐ.ሥ. 17፥18፡32፡34)።

ዛሬም በኢየሱስ የተከናወነው መሰቀሉ፣ መሞቱና መነሣቱ ያስገኘላቸው ታላቅ ደስታና የምሥራች ሲሰበክላቸው እጅግ አቅልለው የሚያዩትና ለእነርሱ እንደማያስፈልግ የሚቈጥሩት ጥቂቶች አይደሉም። አንዳንዶችም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ሲመሰከርላቸውና ወንጌል ሲሰበክላቸው፣ ጌታን በእምነት እንዲቀበሉት ሲነገራቸውም (ዮሐ. 1፥12)፣ የወንጌሉን ቃል ይሰነጥቃሉ፤ በጠዋይ (ጠማማ) አእምሮ ትርጉሙን ያጣምማሉ፤ የት ኼደን ነው የምንቀበለው? በማለትም ስለ መንግሥተ እግዚአብሔር በተሰጠው የዘላለም ሕይወት ብሥራት ላይ ያሾፋሉ (ያፌዛሉ)። እነዚህ ሰዎች የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ጌታ ካልመጡ የዘላለም ፍርድ ይጠብቃቸዋል (ማር. 16፥16፤ ዮሐ. 3፥18፡36)።

በስብከተ ወንጌል ላይ በሰሚዎቹ ዘንድ ብቻ ሳይኾን በሰባኪዎቹም ዘንድ የሚታይ ክፍተት አለ። የስብከተ ወንጌልን ሥራ እግዚአብሔር የሰጠንን ተልእኮ መፈጸም መኾኑን ካላስተዋልን ወንጌልን ለእግዚአብሔር ሰዎችን ማትረፊያ ሳይኾን ለእኛ ሥጋዊ ትርፍ ማስገኛ ልናውለው እንችላለን። ዛሬ በስፋት በየመድረኩ የሚስተዋለውም ይኸው ነው። አንዳንዶቹ ከቃሉ ወጣ ያለ ፍልስፍና የሚመስል ከመጠን ያለፈ ምሳሌና ተረታተረት የበዛበት፣ የሰሚዎቹን አቅምና ኹኔታ ያላገናዘበና የተወሳሰበ፣ የተሰቀለውን ክርስቶስንም ማእከል ያላደረገ ሰብከት  ያቀርባሉ።  አንዳንዶቹ ሰባክያን ደግሞ ራሳቸውን (ጌታ ያደረገልኝ በሚል) እንደ ወንጌል ምስክርነት አድርገው ቢያቀርቡም እጅግ በጣም በማግነን የተሳፈሩበትን አውሮፕላን፣ የኼዱበትን አገር፣ የበሉትን የጠጡትን የለበሱትን ኹሉ ሳይቀር ወንጌል ያልኾነና የተሰቀለውን ክርስቶስን ማእከል ያላደረገ ሰብከት ይሰብካሉ። ሌሎቹም የየሰዉን የልብ ትርታና መሻት በማንበብ “ይሳካልሃል፤  ይኾንልሃል፤ ትጥሳለህ፤ ትጠረምሳለህ፤ ተከናወን…” እያሉ ሰውን በባዶ ተስፋ ይሞላሉ፤ የተሰቀለውን ክርስቶስን ሳይኾን የሰውን ምድራዊ ፍለጎትና መሻት ይሰብካሉ።
  
አንዳንዶቹም “ሰባኬ ወንጌል” የሚል ስም ተሸክመው በየዐውደ ምሕረቱ የሚሰብኩት ግን ወንጌልን አይደለም። የተሰቀለውን ክርስቶስን ገለል አድርገው ቀናት፣ ወራትና  ዓመታት  ተደንግጎላቸው በወንዴና በሴቴ መንፈስ የሚመለኩ አማልክትን (ፍጥረታትን) ለምእመናን ይሰብካሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ሳይኾን አንደበራ (ዲቃላ) መጻሕፍትን ያስተምራሉ። በዚህም በክርስቶስ አዳኝነት አምነው ከመጽደቅና በእርሱ ኖረው መልካም የሕይወትና የአገልግሎት ፍሬ ከማፍራት ይልቅ፣ በኀጢአት ላይ ኀጢአትን በመጨመር ከእግዚአብሔር ባልሆነ ቃል ኪዳን እየተኵራሩ በእገሌ ቃል ኪዳን መሠረት እንዲህ ካደረግሁ  አልኰነንም ብለው የሚያስቡ ምእመናንን ነው የሚያፈሩት። ይህ ኹሉ ከስብከተ ወንጌል ሥራ ውጪ ነው።

የስብከተ ወንጌል ሥራ ግልጽ ነው። ለኀጢአተኛውና መዳን ለሚያስፈልገው ሰው፣ እርሱ ብቻ አዳኝ የኾነውን የተሰቀለውን ክርስቶስን መስበክ፣ በእርሱ እንዲያምንና የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ መንገዱን ማሳየት ነው። እግዚአብሔር ለሰዎች ኹሉ መድኀኒት አድርጎ ከላከው ከተሰቀለው ከክርስቶስ በቀር ሌላ ሌላውን መስበክ ግን የዘላለምን ሕይወት አያስገኝም። ጌታ በደቀ መዛሙርቱ እጅ የላከው “ለዘላለም ድኅነት የኾነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል” (ማር. 16፥8) ነውና ይህን ወንጌል ሳንቀንስና ሳንጨምር፣ ለሰዎች ሕይወት እንዲኾንላቸው በፍቅር፣ በኀይልና በሥልጣንም ልንሰብክ ይገባናል።

በወንጌል የሚበሠረውን የምሥራች በታሪክና በመረጃ ደረጃ የሰሙና የሚያውቁም ኾኑ ያልሰሙና የማያውቁ ሰዎች፣ ወንጌልን ቀለል አድርገው ከማየት ሊወጡና ከኀጢአትና ከዘላለም ሞት ይድኑና ያመልጡ ዘንድ እግዚአብሔር የላከላቸውን መድኀኒት የተሰቀለውን ክርስቶስን ሊያምኑት፣ ሊቀበሉትና ሊድኑበት ይገባል፤ ምክንያቱም ሰው ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጪ የሚኾንበት ዋናው ኀጢአት እግዚአብሔር ለቤዛ ዓለም የላከው ልጁ የእኔም አዳኝ ነው ብሎ አለማመን ነው (ዮሐ. 3፥18፤ 6፥30፤ 16፥9-10)። ስለዚህ ሕይወት የማይገኝበትን ሌላ ሌላውን ወሬ መስማት ትተው፣ ለዘላለም ሕይወት በወንጌል የሚሰበከውን የተሰቀለውን የክርስቶስን አዳኝነት ሊሰሙና በክርስቶስ አምነው የዘላለም ሕይወትን ሊቀበሉ ይገባል።

ዛሬ ለምድራችን እንቈቅልሽ መፍትሔው በወንጌል የሚሰበከው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ሰው ካለበትና ከሚገኝበት ኹኔታ በሚሰበክለት ወንጌል ወደዚህ ጌታ ዘወር ቢል ውስጣዊ ዕረፍት፣ ሰላምና ደስታ ያገኛል። ከውስጡ በሚፈስሰው ዕረፍት፣ ሰላምና ደስታም የምድር ላይ ቈይታውንና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ጤናማና ስኬታማ ሊያደርግ የሚችልበትን አብርሆት ያገኛል። ራሱን ለውጦ ዓለምን የሚለውጥበት የታደሰ አእምሮ ባለቤትም ይኾናል። አዎን መፍትሔው ወንጌል ነው፤ ወንጌልም ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ሮሜ 1፥3-4)።

2 comments:

  1. እግዚአብሔር የተሐድሶውን ሥራ ለክብሩ መገለጥ ለሰዎች መዳን በሚሆን መልክ እየሠራ ስለ ሆነ ምስጋና ለእርሱ ይሁን።

    ReplyDelete
  2. "አንዳንዶቹም “ሰባኬ ወንጌል” የሚል ስም ተሸክመው በየዐውደ ምሕረቱ የሚሰብኩት ግን ወንጌልን አይደለም። የተሰቀለውን ክርስቶስን ገለል አድርገው ቀናት፣ ወራትና ዓመታት ተደንግጎላቸው በወንዴና በሴቴ መንፈስ የሚመለኩ አማልክትን (ፍጥረታትን) ለምእመናን ይሰብካሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ሳይኾን አንደበራ (ዲቃላ) መጻሕፍትን ያስተምራሉ።"
    ጌታ አብዝቶ ይባርካችሁ፤ ይህን ለሰባክያኑ ሁሉ በትምህርት መልክ ቢሰጥ በረከት ይሆናል።

    ReplyDelete