Thursday, October 29, 2020

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

Read PDF

የስብከተ ወንጌል ሥራ እጅግ በመዳከሙና ሰው ኹሉ ከወንጌል ይልቅ ሌሎች ወሬዎችን ወደ መስማት በማዘንበሉ፣ ይልቁንም ከክርስቶስ ወንጌል ወደ ልዩ ወንጌል ፈጥኖ እየገባ በመኾኑ፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ያዘጋጀውን ማዳን ሳይቀበሉ ብዙዎችም ወደ ዘላለም ሞት እየተነዱ በመኾናቸው ይህ ነገር ግድ ያላቸውና ከመናፍስት አምልኮና ከጠላት ዲያብሎስ አሠራር በክርስቶስ ወንጌል ነጻ በወጣው ቤዛ ኵሉ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናነ ወንጌል የስብከተ ወንጌልን ሥራ ለማጠናከር አንድ ጉባኤ አዘጋጅተው ነበር። በዚህ ጉባኤ ላይ እንዲያገለግሉ ከተጋበዙት ሊቃውንትና መምህራነ ወንጌል መካከል አለቃ ነቅዐ ጥብበ አንዱ ናቸው። በዚህ ጉባኤ ላይ ያቀረቡት ትምህርት ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል።

በጉባኤው የመጨረሻ ወይም የማጠቃለያ መርሐግብር ላይ እንዲያገለግሉ የተመደቡት አለቃ ነቅዐ ጥበብ ትምህርታቸውን የመሠረቱበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ 3፥18-20 ያለውን ክፍል አነበቡ፤ ቃሉም እንዲህ የሚል ነው።

“በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ፦ አምላካችሁ እግዚአብሔር ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ሰጥቶአችኋል፤ መሣሪያችሁን ይዛችሁ እናንተ ዐርበኞች ሁሉ በወንድሞቻችሁ በእስራኤል ልጆች ፊት ትሻገራላችሁ። ነገር ግን እጅግ ከብቶች እንዳሉአችሁ ዐውቃለሁና ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ይቀመጣሉ፤ ይኸውም እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፈ፥ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ እነርሱም ደግሞ በዮርዳኖስ ማዶ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ኹሉ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።” (ዘዳ. 3፥18-20)።

ከዚያ አለቃ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር በዚህ ቃል በኩል እንዲናገረን እንጸልይ” አሉና ጉባኤው ተነሥቶ እንደቆም አሳሰቡ፤ ጥቂት የጸጥታ ጊዜ ሰፈነ፤ በዚህ የጸጥታ ጊዜም የጉባኤው ታዳሚ መንፈሱን ለጸሎት አዘጋጀና ከአለቃ ጋር በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ተመመ። ኹሉም አካለ ሥጋው በቤዛ ኵሉ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ ይገኝ እንጂ በመንፈስ ግን እዚያ አልነበረም፤ የዐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ገባባት ወደ ሰማያዊቱ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ በዚያ ተገኝቶ እግዚአብሔርን በእውነትና በመንፈስ ያመልክና ያመሰግን ጀመር።

አለቃም ጸጥታውን ሰብረው ጸሎታቸውን እንዲህ በማለት ጀመሩ፤ “አንተ ብቻ አምላክ፣ አንተ ብቻ ጌታ፣ አንተ ብቻ ፈጣሪ፣ አንተ ብቻ አዳኝ የኾንህ፣ አኰቴትና ክብር፣ አምልኮትና ውዳሴ የተገባህ የአባቶቻችን የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ በተወደደው ልጅህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናመሰግንሃለን። አንተ አባታችን አብርሃምን ከአገሩ፣ ከዘመዶቹና ከአባቱ ቤት የለየኸውና ወዳሳየኸው ምድር ያወጣኸው፣ በኋላም ማርና ወተት የምታፈስሰውን ምድር ለዘርህ እሰጣታለሁ ብለህ ቃል ወደ ገባህለት ምድር ጠርተህ ያወጣኸው፣ የገባኸውን ቃልም በመፈጸም ኹሉን ቻይና ታማኝ አምላክ መኾንህን ያሳየህ ታላቅ አምላካችን ሆይ ስምህ ይመስገን።

“በተነበበውና ከእስራኤል ዘሥጋ ታሪክ ጋር በተገናኘው የአንተ ሕያው ቃል በኩል ዛሬም የምትናገር ሕያው አምላክ እንደ ኾንህ እናምናለን። በዚህ ታሪክ ውስጥ ለሕይወታችን የሚጠቅመንንና የሚረባንን እንድትናገረን እንለምንሃለን። ባሪያህ ሙሴ የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ከሌሎቹ ነገዶች ቀድመው ርስታቸውን ከወረሱ በኋላ፣ እነርሱን እንዳሳረፍሃቸው፥ ወንድሞቻቸውን እስክታሳርፍ ድረስ እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ አንተ የምትሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ርስት ያልወረሱትን ቀሪዎቹን ነገዶች ያግዟቸው ዘንድ መሣሪያቸውን ይዘው በወንድሞቻቸው በእስራኤል ልጆች ፊት እንዲሻገሩ ባዘዛቸው መሠረት ይህን ተልእኮ በታማኝነት እንደ ተወጡ ኹሉ፣ በውድ ልጅህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያዘጋጀኸውን ማዳን ከሌሎቹ ወገኖቻችን ቀድመን እንድናምን የረዳኸንና ልጆችህ ያደረግኸን፣ ወዲህም ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃንህ የጠራኸንን የአንተን በጎነት እንድንነግር የተመረጠ ትውልድ ያደረግኸን እኛም፣ ጌታ ሆይ ወዳዘጋጀኸው ርስት ይገቡ ዘንድ ያላቸውን በጨለማው መንግሥት ውስጥ ለሚገኙት ወገኖቻችን ወንጌልን አብሥረን ወደ ዕረፍታቸው ወደ ኢየሱስ በማምጣት፣ እነርሱም እኛ በእምነት የወረስነውን እንዲወርሱ በማድረግ የወንጌልን ተልእኮ እንፈጽም ዘንድ እንድትረዳን፣ ለወገኖቻችን መዳን ሳንታክትና ሳንሰለች እንድንማልድና እንድንመሰክር ሸክምን እንድትጨምርልን እንለምንሃለን። እግዚአብሔር ሆይ! ወድ ልጅህን ቤዛ አድርገህ ከሰጠህለት ከሰው መዳን የበለጠ አገልግሎት እንደሌለ በልጅህ በክርስቶስ አማካይነት በቃልም በሥራም አሳይተኸናልና እኛም ይህን የአንተን ዋና ጉዳይ ዋና ጉዳያችን እንድናደርግ፣ ከዚህ ውጪ ያሉና ሰዎች ዋና ያደረጓቸውን ኹለተኛ ነገሮች ዋና እናዳናደርግ ማስተዋልን እንድትሰጠን እንለምንሃለን። በአንድ ልጅህ በጌታችን በኢየሱስ ክብርና ምስጋና አምልኮና ውዳሴ፣ ከእርሱ ጋርና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለአንተ ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን!   

ኹሉም ከተቀመጠ በኋላ፣ አለቃ በመጀመሪያ ያነበቡትን የኦሪት ዘዳግም ክፍል ደግመው በማንበብ የዕለቱን መልእክታቸውን ማቅረብ ጀመሩ። “ኦሪት ዘዳግም ስሙ እንደሚያመለክተው በሌሎቹ የኦሪት ክፍሎች የቀረቡትን ሕግጋትና ቃላት፣ የተፈጸሙትን ክሥተቶችም ጠቅለል እያደረገ በድጋሚ የሚያቀርብና የሚያሳስብ መጽሐፍ ነው። ይህ ያነበብሁላችሁ የዘዳ. 3፥18-20 ክፍልም በኦሪት ዘኍልቍ ምዕራፍ 32 ላይ የተፈጸመን ክሥተት የሚያስታውስ ነው። ነቢዩ ሙሴ በዚያ ክፍል የተጠቀሱት የሮቤል የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ የገቡትን ቃል እንዲጠብቁ ዳግም ያሳስባቸዋል።” በማለት መልእክታቸው የተመሠረተበትን የኦሪት ዘዳግም ክፍል ታሪካዊ ዳራን አስጨበጡ። በመቀጠልም “በዚህ ክፍል የተመዘገበው የእስራኤል ዘሥጋ ታሪክ ከእስራኤል ዘነፍስ ታሪክ ጋር የሚነጻጸርበት ብዙ መልክ አለው።” አሉና ይህ ያነበቡት ክፍል የእስራኤል ዘሥጋ ታሪክ ቢኾንም ለእስራኤል ዘነፍስ የሚያስተላልፈው ሕያው መልእክት እንዳለው አመለከቱ።

“ለምሳሌ” አሉ፤ “ለምሳሌ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ እስራኤል ዘሥጋ ምድረ ርስትን በኢያሱ መሪነት መውረሱ፣ እስራኤል ዘነፍስ በክርስቶስ ወደ ዘላለም ዕረፍት ከመግባቱ ጋር ተነጻጽሮ ቀርቧል።” አሉና ምዕራፍ 4 ላይ የሰፈረውን ንጽጽር ይጠቍሙ ጀመር። “በተለይ” አሉ “በተለይ ቍጥር 2 እና 6 ላይ ‘ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምሥራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።’ እንዲሁም ‘እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለ ቀሩ፥ ቀድሞም የምሥራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ’ የሚለው አንዱ ማነጻጸሪያ ነው። በእነዚህ ቍጥሮች ውስጥ ለእስራኤል ዘሥጋም ለእስራኤል ዘነፍስም የምሥራች መሰበኩ፣ ለእስራኤል ዘሥጋ የተሰበከላቸው የምሥራች ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደና የምሥራቹን ቃል ስላልታዘዙ እንዳልጠቀማቸውና ወደ ዕረፍቱ መግባት እንዳልቻሉ ይናገራል። የሚገርመው ለኹለቱም የተሰበከው የምሥራች ነው ተብሏል። ስለዚህ ሐዋርያው እስራኤል ዘነፍስ ከእስራኤል ዘሥጋ ተምረው ለምሥራቹ ቃል በመታዘዝ ወደ ዕረፍቱ የመግባት ዕድላቸውን እንዲጠቀሙበትና ለዚህም እንዲተጉ ያሳስባል።

“ኹለተኛው እስራኤል ዘሥጋን ወደ ምድረ ርስት ከነዓን ያገባውን ኢያሱን፣ እስራኤል ዘነፍስን ወደ ተጠበቀለት ሰማያዊ ዕረፍቱ በማስገባት ከሚያሳርፈው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያነጻጸረበት ነጥብ ተጠቃሽ ነው። “ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢኾንስ፥ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር።” (ቍጥር 8) ይላል። አዎን! በቀን አንጻር “ሌላ ቀን” ተብሎ የተገለጸው ለእግዚአብሔር ሕዝብ የቀረለት አማናዊው ዕረፍት፣ ምድራዊ ሳይኾን ሰማያዊ ነው። ስለዚህ ወደዚህ ፍጹም ወደ ኾነው ዕረፍት የሚያስገባውን በሰማያት ያለፈውን ትልቅ ሊቀ ካህናት የኾነውን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስን በመያዝ ጸንቶ እምነትን መጠበቅ ይገባል ይለናል (ቍጥር 14)።” አሉና በዐይናቸው ጉባኤውን ቃኙ።

ቀጠሉና “ይህን ያስቀደምሁት ቀጥሎ የምናየው የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ታሪክ ከእኛ የመውረስና የማስወረስ አገልግሎት ጋር የሚገናኝበት ገጽታ ያለው መኾኑን እንድታስተውሉ ነው።” በማለት ዋናውን የመልእክቱን ታሪክ ወደ ማሳየትና ከእኛ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ወደ ማብራራት ገቡ።

“ይህ የዘዳ. 3፥18-21 ክፍል ከዮርዳኖስ ወዲህ ማዶ ያለውን ርስት ለተካፈሉት ከ12ቱ ነገደ እስራኤል መካከል ለሮቤል፣ ለጋድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ በድጋሚ የተሰጠ መመሪያ ነው። መነሻ ታሪኩን በዘኍልቍ 32 ላይ እንደምናነበው፣ እነዚህ ኹለት ተኩሉ ነገዶች ለመውረስ የጠየቁት፣ የእስራኤል ነገዶች ኹሉ ዮርዳኖስን ከመሻገራቸው በፊት የነበረውን ምድር በጦርነት ካሸነፉና ታላላቆቹን ነገሥት፦ የሐሴቦንን ንጉሥ ሴዎንን (ዘዳ. 2፥24-37) እና የባሳንን ንጉሥ ዐግን (3፥1-11) ድል አድርገው ከእጃቸው ያስገቡትን ምድር ነው። ምድሩ ለእንስሶቻቸው እጅግ የተመቸ መኾኑን ባዩ ጊዜ ነው ወደ ሙሴ ቀርበው ‘እኛስ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝተን እንደ ኾነ ይህን ምድር ለባሪያዎችህ ርስት አድርገህ ስጠን፤ ወደ ዮርዳኖስም ማዶ አታሻግረን።’ ሲሉ የለመኑት (ዘኍ. 32፥5)።” አሉና አለቃ ጥቂት ዝምታ አሰፈኑ።

“እኒህ ኹለት ተኩል ነገዶች” አሉ ገጽታቸው ላይ አንክሮታዊ ትእምርት እየተነበበ “ምን ዐይነት ብልኆች ናቸው? … ምን ዐይነት ፈጣኖች ናቸው? … ምን ዐይነትስ ጮሌዎች ናቸው? … ምን ዐይነት ለራሳቸው የሚያስቡ ናቸው? ልንል እንችላለን። መጀመሪያ የተገኘውን ርስት ቀድመው ለመካፈልና የራሳቸው ለማድረግ ከሌሎቹ ዘጠኝ ተኩል ነገዶች ይልቅ ዐይኖቻቸው የተከፈቱላቸው ናቸው። ሌሎቹ ነገዶች ይህን ጥያቄ ሳያነሡ እነርሱ ቀድመውና ፈጥነው ማንሣታቸው ይገርማል።

“እንደሚታወቀው ይህ ከዮርዳኖስ ወዲህ ማዶ የተገኘው ድል በኋለኛው ዘመን እስራኤል ብዙ ቅኔ የተቀኙበት፣ ብዙ ምስጋናም ያቀረቡበት ድል ነው።

ብዙ አሕዛብን መታ፥

ብርቱዎችንም ነገሥታት ገደለ።

የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥

የባሳንንም ንጉሥ ዐግን፥

የከነዓንን መንግሥታት ሁሉ ገደለ፤

ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ለእስራኤል ለሕዝቡ ርስት ሰጠ።’ (መዝ. 135፥11) ተብሎለታል።

“እንዲሁም፦ ‘ታላላቅ ነገሥታትን የመታ፤

     ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

     ብርቱዎችንም ነገሥታት የገደለ፤

     ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

     የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፤

     ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

     የባሳንን ንጉሥ ዐግን፤

     ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

     ምድራቸውን ርስት አድርጎ የሰጠ፤

     ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

     ለባሪያው ለእስራኤል ርስት፤

            ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።’ (136፥20) ተብሎም ለድሉ ባለቤት ለእግዚአብሔር ስለ ዘላለማዊ ምሕረቱ ክብርና ምስጋና ተሰጥቷል። እነዚህ ኹለት ተኩል ነገዶች ለመውረስ ጥያቄ ያቀረቡበት ይህ ምድር እንዲህ ዐይነት ቅኔና ምስጋና የፈሰሰበትን ድል ያስገኘ ምድር ነው።

“የተሰጠን ርስት ለመውረስ መዘግየት እንደማያስፈልግ ከእነዚህ ነገዶች ትልቅ ትምህርት እንማራለን። በጦርነት የተለቀቀውን ምድር ሊወርሱ የሚችሉት ከዐሥራ ኹለቱ ነገደ እስራኤል መካከል የኾኑቱ ናቸው። ምናልባት የቀሩቱ ‘እናንተ ይህን ውረሱ’ እስኪባሉ እየጠበቁ ይኾናል፤ ለመውረስ የፈጠኑትና እንውረስ ያሉት ግን የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ናቸው። ዛሬም በክርስቶስ የተዘጋጀውን ርስት እንዲወርሱ ለሰዎች የምሥራቹ ሲሰበክላቸው የሚያመነቱ፣ ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ የሚሰጡ፣ ገፋ ሲልም ለምን ነገርኸኝ? ብለው የሚጣሉና የሚሳደቡ ጥቂቶች አይደሉም። ነገር ግን የምሥራቹ ቃል ሲሰበክ ፈጠን ብሎ ማመን፣ ለአዳኙ ለኢየሱስ የልብን በር ወለል አድርጎ መክፈትና እርሱን ወደ ሕይወት ማስገባት ያስፈልጋል፤ የመዳን ቀን አኹን ነውና።

“ልብን ለጌታ ከመክፈት መዘግየት ምን ያኽል ዋጋ እንደሚያስከፍል በማሕልየ መሓልይ ውስጥ የምናገኛት የሙሽራዪቱ ነገር ጥሩ ምሳሌ ነው። እርሷ ልቧ ነቅቶ ግን ተኝታ ሳለ ውዷ በሌሊት መጥቶ፣ በውጪ ቆሞ ‘እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ ሆይ፥ በራሴ ጠል፥ በቈንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈቺልኝ’ እያለ ደጁን ሲመታ፣ ‘ቀሚሴን አወለቅሁ፤ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ፤ እንዴት አሳድፈዋለሁ?’ የሚሉ ሰበቦችን በመደርደር ላለመክፈት ስታመነታ ቈይታ ከብዙ ማመንታት በኋላ ተነሥታ ብትከፍትለት ውዷ ፈቀቅ ብሎ ዐልፎ ነበር። መጥቶላት የነበረውን ለውዷ በቶሎ ከፍታ ማስገባት ባለመቻሏ፣ አኹን በተራዋ ዐልፎ የኼደውን ውዷን ፍለጋ በሌሊት ወጣች። ከተማይቱን የሚዞሩ ጠባቂዎች አግኝተው፤ መቷት፥ አቈሰሏት፤ ቅጥር ጠባቂዎችም የዐይነ ርግብ መሸፈኛዋን ወሰዱባት። ውዷን ፍለጋ ብዙ ተንከራተተች፤ ከፍቅር የተነሣም ታመመች (5፥1-8)። ዛሬም የልባቸው በር በወንጌል ቃል ሲንኳኳ ለጌታ ለመክፈት የተለያየ ምክንያት የሚደረድሩና ከመክፈት የሚዘገዩ ከእርሷ መማር አለባቸው።” አሉና ቃሉን ከአድማጮቻቸው ሕይወት ጋር ከማዛመድ ወጥተው ወደ ኹለት ተኩሉ ነገዶች ታሪክ ተመለሱ።      

“የእነዚህ የኹለት ተኩሉ ነገዶች ይህን ምድር ለእኛ ስጠን? የሚለው ጥያቄያቸው በመጀመሪያ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ከሙሴ በኩል ነበር (ዘኍ. 32፥6-15)። ሙሴ ለመቃወም የበቃው የእነርሱ ጥያቄ አለጊዜው የቀረበና ከፊቱ ዮርዳኖስን መሻገርና ብዙ ጦርነት አድርጎ ርስቱን መውረስ የሚጠበቅበትን የዘጠኝ ተኩሉን ነገደ እስራኤል ልብ የሚያዳክም ጥያቄ ኾኖ ነው በማግኘቱ ነው። ስለዚህ ‘ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ በዚህ ትቀመጣላችሁን? እግዚአብሔር ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ የእስራኤልን ልጆች ልብ ለምን ታደክማላችሁ?’ (ቍጥር 6፡7) ሲል በጽኑ ተቃወማቸው። ድርጊታቸውንም ከዚህ ቀደም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ርስት አድርጎ ይሰጣት ዘንድ ለአብርሃም ተስፋ የገባለትን ምድረ ከነዓንን እንዲሰልሉ ከተላኩት ዐሥራ ኹለት ሰዎች መካከል ከዐሥሩ ድርጊት ጋር ነው ያመሳሰለው። እነርሱ የሕዝቡን ልብ በማድከም የእግዚአብሔር ቍጣ እንዲነድድና ያ ትውልድ አርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲቅበዘበዝ፣ ከኢያሱና ከካሌብ በቀርም የተስፋዪቱን ምድር እንዳያዩ እንዳደረጉ ኹሉ እነዚህም እንዲሁ ማድረጋቸውን እንዲህ በማለት ገለጸ፦ ‘እነሆም፥ የእግዚአብሔርን መዓት በእስራኤል ላይ አብዝታችሁ ትጨምሩ ዘንድ እናንተ የኀጢአተኞች ትውልድ በአባቶቻችሁ ፈንታ ቆማችኋል። እርሱን ከመከተል ብትመለሱ እርሱ ሕዝቡን በምድረ በዳ ደግሞ ይተዋል፤ ይህንም ሕዝብ ኹሉ ታጠፋላችሁ።’ (ቍጥር 14፡15)።

“እውነት ነው፤ ሙሴ ክፉኛ የተቈጣባቸው የሮቤል የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ያቀረቡት የመውረስ ጥያቄ ከፊቱ ብዙ ጦርነት የሚጠብቀውን የሕዝቡን ልብ የሚያዝል መስሎ ቢታይም፣ እነርሱ ግን ሙሴን ለዚህ አታስብ፤ አንተ ያልኸው እንዳይደርስ እኛ መፍትሔ አለን አሉ። ይህን ምድር ስጠን እንጂ፦

·         በምንወርሰው በዚህ ምድር ለእንስሶቻችንና ለልጆቻችን ከተሞችን እንሠራለን፤

·         እነርሱን በተመሸጉ ከተሞች አስቀምጠን እኛ ግን የእስራኤል ልጆች ኹሉ ርስታቸውን እስኪወርሱ ድረስ ወደ ቤቶቻችን አንመለስም፤

·         ከዮርዳኖስ ወዲያ ማዶም ርስት አንወርስም አሉ (ዘኍ. 32፥16-19)።

ይህም ንግግራቸው ሙሴን ደስ አሰኘው። ቃላቸውን ጠብቀው ያሉትን ቢፈጽሙ ከአፋቸው የወጣውንም ነገር ቢፈጽሙ፣ በእግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆችም ፊት ንጹሓን እንደሚኾኑ፣ ለመውረስ የጠየቋት ምድር በእግዚአብሔር ፊት ርስት እንደምትኾንላቸው፣ ቃላቸውን ባይጠብቁ ግን እግዚአብሔርን እንደሚበድሉና ኀጢአታቸውም እንደሚያገኛቸው በግልጽ ነገራቸው። እነርሱም የተናገሩትን እንደሚፈጽሙ ለሙሴ አረጋገጡ። ‘ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ግዛት፥ ምድሪቱንና በዙሪያዋ ያሉትን ከተሞች ሰጣቸው።’

“ቅድም በመጀመሪያ ያነበብሁት ኦሪት ዘዳግም 3፥18-21፣ አኹን በኦሪት ዘኍልቍ ያየነውን የዚህን ታሪክ ዝርዝር ኹኔታ መሠረት አድርጎ በድጋሚ የሚያቀርብና እንደ ገና የሚያሳስብ መመሪያ ያለበት ነው። መመሪያው ዳግም የተሰጣቸው የሮቤል የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ እንዲያደርጉ የተፈለገው ኹለት ነገሮችን ነው።” በማለት ምን ምን እንደ ኾኑ ነጥብ በነጥብ መናገር ቀጠሉ። “የመጀመሪያው” አሉ አለቃ “የመጀመሪያው ‘እጅግ ከብቶች እንዳሉአችሁ ዐውቃለሁና ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ይቀመጣሉ፤’ የሚል ነው። ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ከመኼዳቸው በፊት አስቀድመው የራሳቸውን ርስት የማጠናከር ሥራ እንዲሠሩ የሚያሳስብ ነው።” አሉ። ቀጠሉና “ኹለተኛው መመሪያ ደግሞ ቍጥር 18 እና 20 ላይ ‘መሣሪያችሁን ይዛችሁ እናንተ ዐርበኞች ኹሉ በወንድሞቻችሁ በእስራኤል ልጆች ፊት ትሻገራላችሁ። … ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ እነርሱም ደግሞ በዮርዳኖስ ማዶ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ’ እንዳለ ስለ ወንድሞቻቸው እንዲዋጉ ነው። ከዚህ ምን እንማራለን? አሉና የጉባኤው ታዳሚ ለራሱ ሊመልሰው የሚገባውን ጥያቄ አቀረቡ። መልሱን ከጉባኤው ታዳሚ ሳይጠብቁ ልንማረው የሚገባ ያሉትን ነጥብ ወደ ማቅረብ ገቡ።

“ከዚህ የምንማረው ምንድነው? … አዎን! እንደ እስራኤል ዘነፍስ ወይም እንደ ሐዲስ ኪዳን አማኞች ከዚህ የምንማረው ከመዳናችን ጋር የተገናኘውን ጕዳይ ነው። የመዳን ወንጌል የበራልን ሰዎች በመጀመሪያ ማድረግ ያለብን የራሳችንን መዳን መፈጸም ነው። እነዚያ ኹለት ተኩል ነገዶች ‘በዚህ ለእንስሶቻችን በረቶች ለልጆቻችንም ከተሞች እንሠራለን፤ … በዚህም ምድር ስላሉ ሰዎች ልጆቻችን በተመሸጉ ከተሞች ይቀመጣሉ።’ (ዘኍ. 32፥16፡17) ብለው እንደ ተናገሩ፣ እኛም በቅድሚያ ክርስቶስ የሞተለትን ሕይወታችንን በቅድስና መጠበቅና ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ መኖር አለብን። ወይም በመጀመሪያ የራሳችንን ድኅነት ማረጋገጥ አለብን። ይህም ማለት ወንጌል የበራለን፣ ሕይወታችን በበራልን ወንጌል የተለወጠ መኾኑን በኑሯችን ማሳየት አለብን ማለት ነው። በኹለተኛ ደረጃ ይህን እኛ በእምነት የተቀበልነውን ሕይወት ሌሎችም ያገኙ ዘንድ ለእነርሱ የምሥራቹን ቃል ወይም ወንጌልን ማብሠር ነው። ማብሠር ብቻም አይደለም፤ በቃልም በኑሮም ወንጌልን መስበክ ይገባናል። እግዚአብሔር እኛን በክርስቶስ እንዳሳረፈን በክርስቶስ ያላረፉ ብዙ ወገኖቻችን በክርስቶስ አምነው እስኪያርፉ ድረስ ስለ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን መዳን መጋደል አለብን። በክርስቶስ የዳነ ሰው ድኛለሁ ብሎ በራሱ መዳን እየተደሰተ ብቻ አይኖርም፤ የራሱን መዳን እየፈጸመ፣ ለሌሎች መዳን ይኖራል። ይህ የሕይወት ዘመን ሥራ ነው። እኛ ዛሬ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን በእምነት ወደ ወረስነው ርስት የምንገባው በዚህ ምድር ላይ ባለን ቈይታ ሌሎቹ ክርስቶስ የሞተላቸውና ይህ ርስት የተጠበቀላቸው ወገኖቻችን ወደ ርስታቸው ካስገባን በኋላ ነውና እስከዚያው ተግተን ስለ ወንድሞቻችን መንፈሳዊውን ጦርነት እንዋጋ።

“ቀጥሎ ምን ኾነ?” አሉ አለቃ በንቃት እየተከታተላቸውና የኹለት ተኩሉን ነገድ ሕይወት ከራሱ ጋር እያዛመደ ያለውን የጉባኤውን ታዳሚ ወደ ሌላው ነጥብ ለማሸጋገር፣ “ቀጥሎ የኾነው ይህ ነው። እነዚህ ኹለት ተኩል ነገዶች ርስታቸውን ከተቀበሉ በኋላ እንደ ተናገሩት የተመሸጉ ከተሞችን ሠርተው ሚስቶቻቻውንና ልጆቻቸውን ከብቶቻቸውንም በዚያ አስቀምጠው ወደ ጦርነቱ መውጣት አለባቸው። ሙሴም በዘዳግም ላይ በድጋሚ እንዳሳሰባቸው ኹሉ፣ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከሞተ በኋላ ደግሞ በእርሱ እግር የተተካው ኢያሱ በተመሳሳይ መንገድ ሲያሳስባቸው እናያለን። አሉና መጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ አንድ ላይ ያለውን ክፍል ማውጣት ያነብቡ ጀመር፦

“ኢያሱም የሮቤልን ልጆች የጋድንም ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ እንዲህ ብሎ ያዘዛችሁን ቃል ዐስቡ፦ አምላካችሁ እግዚአብሔር ያሳርፋችኋል፥ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል። ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በሰጣችሁ ምድር ይቀመጡ፤ ነገር ግን እናንተ፥ ጽኑዓን ኃያላን ኹሉ፥ ተሰልፋችሁ በወንድሞቻችሁ ፊት ተሻገሩ፥ እርዱአቸውም፥ እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፋችሁ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ፥ እነርሱም ደግሞ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ፤ ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በፀሓይ መውጫ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ትመለሳላችሁ፥ ትወርሱአትማላችሁ። እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ብለው መለሱለት፦ ያዘዝኸንን ነገር ኹሉ እናደርጋለን፤ ወደምትልከንም ስፍራ እንሄዳለን። በሁሉም ለሙሴ እንደ ታዘዝን እንዲሁ ለአንተ ደግሞ እንታዘዛለን፤ ብቻ አምላክህ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን።” (ኢያ. 1፥12-17)።

 

አለቃ ዐይኖቻቸውን በጉባኤው ላይ ተክለው ጥቂት ጸጥ ካሉ በኋላ “እነዚህ ኹለት ተኩል ነገዶች ቃላቸውን ለመጠበቅ ምን ያኽል ትጉዎች እንደ ኾኑ ተመልከቱ።” አሉ። በመቀጠልም “በዚህ ወቅት በፊቱ ቃል የገቡለት ሙሴ በመካከላቸው በአካለ ሥጋ አልነበረም፤ ሞቷል። የገቡት ቃል ግን አለ፤ መፈጸምም አለበት። ስለዚህ እዚያ ላይ አተኵረው ቃላቸውን እንደ ገና ሲያጸኑና ወንድሞቻቸውን ለማሳረፍ በሚደረገው ጦርነት ኢያሱ ወደሚልካቸው ስፍራ ኹሉ ለመኼድ ዝግጁ እንደ ኾኑ ሲናገሩ በቃሉ ውስጥ እናነባለን።

“በክርስቶስ በማመን የዘላለምን ሕይወት የተቀበሉ ምእመናንን ስለ ወንጌል ተልእኮ ደግመን ደጋግመን መናገር፣ ማሳሰብ አለብን።” አሉ አለቃ ከዚህ ነጥብ መወሰድ ያለበትን ትምህርት በማስገንዘብ። “እውነት ነው! ለሮቤል፣ ለጋድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፣ ሙሴ በድጋሚ አንድ ጊዜ ስለ ወንድሞቻቸው መዋጋት ያለባቸው መኾኑን አስገንዝቧቸዋል። እርሱ ካለፈ በኋላ ደግሞ ተተኪው ኢያሱ ሕዝቡን መምራት እንደ ጀመረ ለሕዝቡ አለቆች ሕዝቡን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ለመግባት እንዳዘጋጁ ካዘዘ በኋላ፣ ለሮቤል ለጋድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ለኹለተኛ ጊዜ አሳሰባቸው።

“በምንገኝበት በዚህ ዘመን ከወንጌል ተልእኮ የሚያስወጡና በልዩ ልዩ ዓለማዊና መንፈሳዊ መሰል ጕዳዮች የሚጠምዱ በርካታ ነገሮች ይገኛሉ። ዓለማዊውን ነገር እናቈየውና መንፈሳዊ በሚባለው አካባቢ እንኳ እውነተኛው ወንጌል ሳይኾን፣ “ልዩ ወንጌል” በልዩ ልዩ መልክ ማለትም በስኬት፣ በፈውስና በመሳሰለው ሰው በሚፈልገው መንገድ እየቀረበና ሰውን ወደ እግዚአብሔር ሳይኾን ወደ ገዛ ምኞቱና ወደ ሕልሙ ዓለም እያስገባው፣ የሌለውን አገኝ ብሎ ያለውን እያሳጣው፣ እንዲሁ ሊቀበለው የሚገባውን ነጻ የፈውስ ስጦታ በገንዘቡ፣ ለዚያውም በአብዛኛው ተመሳስሎ የቀረበውን “የፈውስ ስጦታ”፣ እየገዛ ይገኛል። ፈዋሹን ጌታ ሳይኾን አገልጋዮችን ለማምለክ እስኪካጣው ድረስ ዐይኖቹ ወደ ጌታ ማየት ትተው ሰው ላይ ዐርፈዋል። ይህ ኹሉ እውነተኛው የወንጌል ተልእኮ ቸል መባሉንና ለልዩ ወንጌል ትኵረት መስጠቱን ያሳያል። ስለዚህ እውነተኛውን የወንጌል ተልእኮ ደግሞ ደጋግሞ ማስገንዘብና ማሳሰብ ይገባል። ለእኛም ስለ ወንጌል መኖር፣ ወንጌልን ላልሰሙት የማሰማት ጉዳይ ተደጋግሞ ሊነገረን፣ እኛም ደጋግመን ቃል ልንገባና ለወንጌል የሚገባውን ልናደርግ ይገባል። እውነተኛው የወንጌል ተልእኮ ሌላ አይደለም፤ እኛ በክርስቶስ በማመን ወደ ገባንበት ዕረፍት ወገኖቻችንም በማመን እንዲገቡ ስለ እነርሱ መንፈሳዊውን ተጋድሎ ማድረግ ነው። ይኸውም ስለ እነርሱ መማለድ፣ ለእነርሱ ወንጌልን መስበክ፣ ወደ እነርሱ የወንጌል ልኡካንን መላክ፣ እንዲህ ያለውን አገልግሎት መደግፍ ወዘተ. ይገባል።” አሉና አለቃ ለኹለቱ ተኩል ነገድ በተደጋጋሚ የተላለፈው ማሳሰቢያ ከዚህ ዘመን የወንጌል ተልእኮ ጋር እንዴት እንደሚገናኝ አስገነዘቡና ወደ ተከታዩ ነጥብ ዐለፉ።               

“እነዚህ እስካኹን በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ የተሰጣቸው የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ከዚህ ኹሉ ማሳሰቢያ በኋላ ምን አደረጉ? ተልእኮአቸውን ተወጡ? ወይስ አልተወጡም? የሚሉት ነጥቦች ወሳኝ ነው።” አሉና አድማጮቻቸው በንቃት እንዲያደምጡ የሚያደርግ ነጥብ አነሡ። የኹሉም ዐይንና አፍ ተከፍቶ አለቃ ቀጥሎ የሚናገሩትን ለመስማት መጓጓቱ ከፊቱ ላይ ይነበብ ነበር። አለቃ ቀጠሉ “እነዚህ ኹለት ተኩል ነገዶች በራሳቸው ርስት ላይ የተመሸጉ ከተሞችን፣ ለከብቶቻቸው በረቶችን ከሠሩ በኋላ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን እዚያ ካስቀመጡ በኋላ ቃላቸውን ጠብቀው በእስራኤል ልጆች ፊት ዮርዳኖስን በመሻገር ስለ ወንድሞቻቸው ተዋጉ፤ ወንድሞቻቸው እስራኤል ኹሉ ርስታቸውን እንዲወርሱም ረዷቸው፤ ኹሉ ከዮርዳኖስ ወዲያ ማዶ የተሰጣቸውን ርስት በጦርነት ወረሱ። ይህ በአንድ ጊዜ ጦርነት ብቻ የኾነ አይደለም፤ በርካታ ዓመታት ፈጅቷል፤ በእነዚህ ዓመታት ኹሉ እነዚህ ኹለት ተኩል ነገዶች ወደ ቤታቸው አልተመለሱም፤ ለጦርነት እንደ ወጡ ነው፤ ምናልባት በዚህ ጦርነት ላይ የቈሰሉና እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ዋጋ የከፈሉም ይኖራል።

ከዚህ በኋላ ነበር ኢያሱ እነዚህን ነገዶች ጠርቶ ቃላቸውን ጠብቀው ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ተዋጉና እንዲወርሱ ስለ ረዷቸው አመስግኖና መርቆ ወደ ርስታቸው የሸኛቸው። በመጽሐፈ ኢያሱ ኢያ. 22፥1-8 የተጻፈውን እስኪ እንስማ አሉና መጽሐፍ ቅዱሱን ገለጥ ገለጥ አደረጉና ማንበብ ጀመሩ፦

“በዚያን ጊዜም ኢያሱ የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ጠብቃችኋል፥ እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል ይህንም ያህል ብዙ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቃችኋል። አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፤ አሁን እንግዲህ ተመለሱ፥ ወደ ቤታችሁና የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ሂዱ። ብቻ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ታደርጉ ዘንድ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ መንገዱንም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጠጉ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩ ዘንድ እጅግ ተጠንቀቁ። ኢያሱም መረቃቸው፥ ሰደዳቸውም፤ ወደ ቤታቸውም ሄዱ። ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ በባሳን ውስጥ ርስት ሰጥቶአቸው ነበር ለቀረው ለእኩሌታው ግን ኢያሱ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ ወገን በወንድሞቻቸው መካከል ርስት ሰጣቸው። ኢያሱም ወደ ቤታቸው በሰደዳቸው ጊዜ እንዲህ ብሎ መረቃቸው፦ በብዙ ብልጥግና በእጅግም ብዙ ከብት፥ በብርም፥ በወርቅም፥ በናስም፥ በብረትም፥ በእጅግም ብዙ ልብስ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ የጠላቶቻችሁንም ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ።” አለቃ ንባቡን እንደ ገቱና ወዲያው “ክብር ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ይኹን” በማለት እግዚአብሔርን ባረኩ። ጉባኤውም አሜን በማለት ባሪያዎቹን የረዳውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ። “ወርሶ ማውረስ፣ ተልእኮን ፈጽሞ ወደ ርስት መግባት እንዴት ደስ ይላል!” አሉ አለቃ ውስጣቸው ሐሤት እያደረገ።

“ወገኖቼ ተልእኮአችንን ምን ያኽል እየፈጸምን ነው?” በማለት ጉባኤውን ጠየቁ። “ልብ በሉ! እዚህ ምድር ላይ ያለነው ዛሬ ብዙዎች በልዩው ወንጌል ተወስደው እንደሚያስቡት የጌታ ዕቅድና ዐላማ እኛን ምድር ላይ እያቀማጠለና እያንደላቀቀ ለማኖር ወይም ለራሳችን ብቻ ለመኖር አይደለም፤ ኢየሱስ የሞተላቸውን ሰዎች ወደ መንግሥቱ ልናስገባ ነው እንጂ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ውስጥ ወዳገለገለው ጌታ በመኼድና (በሞተ ሥጋ ተለይቶ) እዚህ ምድር ላይ በመቈየት መካከል ኾኖ ‘… በሥጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢኾን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። በእነዚህም በኹለቱ እጨነቃለሁ፤ ልኼድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከኹሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው።’ ብሏል (ፊል. 1፥22-24)። በዚህ መሠረት የእኛንም በሥጋ መኖር ስናስብ፦  

·         በሥጋ መኖራችን ለእኛ የሥራ ፍሬ ነው፤

·         በሥጋ መኖራችን ለሌሎች የሚያስፈልግ ነው።

“እንደ ኹለት ተኩሉ ነገድ ለወገኖቻችን ተዋግተንና ወደ ርስታቸው አስገብተን እኛም አስቀድሞ በእምነት ወደ ገባንበት ርስት የምንኼደው በብዙ ፍሬና በረከት ነው። የሕይወት አክሊል ተዘጋጅቶልናል። ይህን አክሊል የምንቀበልባቸው ዛሬ በወንጌል አገልግሎት የምናፈራቸው ፍሬዎች ናቸው። ይህን አስመልክቶም ሐዋርያው “ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክሕታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን?” (1ተሰ. 2፥19) ይላል።

ስለዚህ ወገኖቼ አኹን ያለው የምድራችን ምስቅልቅል ኹኔታ እንዲሁም ልዩው ወንጌል አዘናግተውን የጣልነውንና የዘነጋነውን የወንጌል ተልእኮ እንደ ገና ከጣልንበት ማንሣትና ክርስቶስ ተወልዶላቸው ልደቱን እያከበሩ በመወለዱ የተደረገላቸውን ደስታ ሳይቀበሉ በሐዘን ውስጥ ለሚኖሩት የምሥራቹን ማብሠር አለብን። ክርስቶስ ተሰቅሎላቸው ስቅለቱን በዓል አድርገው እያከበሩና ስቅለቱን በትልቅ ሐዘን እያሰቡ ነገር ግን ለኀጢአታቸው የተከፈለ ዕዳ አድርገው በማመን ከኀጢአትና ከሞት ባርነት ነጻ መውጣት ላልቻሉት የምሥራቹን ማብሠር አለብን። ክርስቶስ ከሙታን መነሣቱን አውቀው በዓለ ትንሣኤውን በደስታ በመብልና በመጠጥ እያከበሩ ከእርሱ ጋር በእምነት ሳይነሡና በሰማያዊ ስፍራ ሳይቀመጡ ክርስቶስ ሊያጸድቃቸው መነሣቱን ሳያስተውሉ አኹንም በኵነኔ ውስጥ እንዳሉ ለሚሰማቸው ወገኖቻችን ‘ኢየሱስ ሊያጸድቃችሁ ተነሥቷል’ ብለን የምሥራቹን ልናበሥራቸው ይገባል። እግዚአብሔር አምላካችን ልባችንን በልጁ የመስቀል ፍቅር ያቀጣጥልልን፤ በልባችን ውስጥም ወደ ሞት የሚነዱትን ሰዎች ለመታደግ ሸክምን ይጨምርልን።”

3 comments: