Read IN PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 1፣ ላይ የቀረበ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ መሠረትነት ላይ ያቋቋማትን የእግዚአብሔር መንግሥት (መንግሥተ ሰማያት) እድገት የሚገልጽ ምሳሌ ሲናገር እንዲህ አለ፡፡
“መንግሥት ሰማያት ሰው ወስዶ በዕርሻ የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣትን ትመስላለች፡፡ እርስዋ ከዘር ሁሉ ታንሳለች ባደገች ጊዜ ግን ከአትክልቶች ሁሉ ትበልጣለች፥ የሰማይ ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ የሚሰፍሩባት ዛፍ ትሆናለች” (ማቴ.13፥31-32)፡፡
የእግዚአብሔር በግ ሆኖ በመስቀል ላይ ተሠውቶ ደሙን በማፍሰሱ ምክንያት ኀጢአት ከእግዚአብሔር የለየውን የሰው ልጅ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ኀጢአትን ተከትሎ ወደ ዓለም ገብቶ በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣኑን ያሰፈነውን ሞት በትንሣኤው ከሻረ በኋላ በክብር ወደ ሰማያት ዐረገና በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ፡፡ እግዚአብሔር በጸጋው የሠራውንና በልጁ በኵል የተገለጸውን ሰውን የማዳን አስደናቂ ሥራ የተቀበሉና ለዓለም ሊመሰክሩ ራሳቸውን ያዘጋጁ የመጀመሪያዎቹ ምእመናን ቊጥር 120 ያህል ነበር (ሐ.ሥ. 1፥13-15)፡፡
በትንቢተ ኢዩኤል የተገለጸውና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሰጠን ቃል የገባልን ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እነዚህን 120 አማኞች በተጎዳኛቸው ጊዜ 3000 አማኞች በአንድ ጊዜ መጨመራቸውን የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ መዝግቦታል (ሐ.ሥ. 2፥1-42)፡፡
በሕግ፥ በመዝሙራት፥ በትንቢተ ነቢያት ንድፈ ሐሳቡ ሲሰበክ ቈይቶ፥ በጊዜው ይፋ የወጣውን የእግዚአብሔር መንግሥት ዐዋጅ ብሉይ ኪዳን የእምነት መመሪያችን ነው የሚሉ አይሁድ አለመቀበላቸው ሳያንሳቸው በግልጽ ተቃወሙት (ሮሜ ምዕራፍ 9 እና 10)፡፡
ዳሩ ግን የእግዚአብሔር መንግሥት (መንግሥተ ሰማያት) እጅግ ፈጣን በሆነ ግስጋሴ ኢየሩሳሌምን፥ ይሁዳን፥ ሰማርያን … እያዳረሰች በማለፍ፥ ከምድረ እስራኤል ውጪ በየአቅጣጫው ቅርንጫፎችዋን አንሰራፋች፤ አድማስንና ዘመንንም ሰንጥቃ ከእኛ ዘንድ ደረሰች (የሐዋርያት ሥራን፥ በተለይም ኢትዮጵያን በሚመለከት ምዕራፍ 8፥4-40 ይመልከቱ)፡፡
የእግዚአብሔር መንግሥት ከዘመናችን ትውልድ ዘንድ ለመድረስ በረሓ፥ ጫካ፥ ድንጋይ፥ ማጥ … ያለበትን ዳገትና ቊልቊለት፥ ስርጓጕጥና ሻካራ የሆነ ረጅም የታሪክ መንገድ ተጕዛለች፡፡ በአይሁድ፥ በአረማውያን በመናፍቃን … ከተሰነዘረባት ጥቃት አምላክ ጠብቋታል፡፡
“ክርስትና በኢትዮጵያ” በሚለው ርእስ የሚቀርበው ታሪክ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የተቋቋመችው ያንዲት የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ ክፍል እንደ ሆነ ግልጽ ነው ስለ ሆነም የሀገራችንን የክርስትና እምነት ታሪክ በየዘመኑና በየክፍለ እርከኑ ከፋፍለን ስናጠና በንጽጽሩ ክፍለ ዘመንም ሆነ የታሪክ እርከን በሌሎቹ የዓለም ክፍሎች በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ከተከናወኑት ወይም ከተከሠቱት ዐበይት ክንውኖችና ክሥተቶች በጣም ጐልተው የሚታወቁትን ብቻ በመጠኑ መዳሰሳችን አይቀርም፡፡
ይህ ዐይነቱ አቀራረብ የተለመደ የታሪክ አጻጻፍ ፈሊጥ ከመሆኑ ጋር የኛውንና የሌላውን ክንውንና ድክመት አንባቢ እያነጻጸረ በሚፈልገው መንገድ ሁኔታዎችን ሊገመግመበትና ሊያመዛዝንበት፤ ጥያቄና መልሶችን ሊያዘጋጅበት የሚያስችል ይሆናል፡፡
በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ አብዛኛውን የታሪክ ክፍል የሚይዘው በየአቅጣጫው በምእመናን ላይ የደረሰው ስደት እንደ ሆነ ይታወቃል፡፡ ክርስትና ያን ያህል የሕይወት፥ የደም፥ የሀብት፥ የትዳርና የሌላውም ማኅበራዊ ኑሮ … መሥዋዕትነት የተከፈለበት እንደ ሆነ ስንመለከትም በአርኣያነቱ የእኛን የእምነት ጥንካሬ እንለካበታለን፡፡
ያለፉትን ረጅም ዓመታት በማቋረጥ በቅብብሎሽ (በትውፊት) የክርስትናን እምነት እኛ ዘንድ ለማድረስ ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በመሣሪያነት የተጠቀመባቸውን ቅዱሳን አባቶች ውለታ በአንድ በኩል ሲያስታውሰን በሌላ መልኩ ለተከታዩ ትውልድ ልናስተላልፍለት የሚገባውን እንድናዘጋጅ የታሪኩ ጥናት ይቀሰቅሰናል፡፡
በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ለእግዚአብሔር መንግሥት ምሳሌ ካደረጋት፥ ራሱ ባለቤቱ ዘርቶና አብቅሎ ካሳደጋት ከሰናፍጯ ዛፍ ይልቅ የተንሰራፉትን የሐሰተኛ ትምህርት ዐረሞች በታሪኩ ውስጥ መቼና በማን እንደ ተዘሩ እንመለከታለን፡፡ በየዘመኑ የተዘሩት ሐሰተኛ ትምህርቶች የሰናፍጯን ዛፍ በመተብተብና እርሷን በመዋጥ ራሳቸውን አጕልተው ስናያቸው “በአባቱ ከተማ ልጁ ተቀማ” የሚለውን የአበው ምሳሌና በወንጌል “ጌታ ሆይ አንተ የዘራኸው ስንዴ ብቻ አልነበረምን? እንክርዳዱ ከየት መጣ?” የተባለውን ኀይለ ቃል እሙንነት ያስረዳናል፡፡
ከእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በተለይ ክርስትና በኢትዮጵያ የተሰኘውን ክፍል ማወቃችን፥ ያወቅንም ብንሆን መከለሳችን እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን ውለታ እንድናስታውስ የሚረዳን ስለ ሆነ በዚህ መጽሔት በተከታታይ የሚቀርብ መሆኑን ለአንባብያን ስንገልጽ በፍጹም ትሕትና ነው፡፡
ጮራ መጽሄትን በሚገባ አውቃታለሁ፡፡ ብዙ መንፈሳዊ እውቀትም አግኝቼባታለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ድረገጽ ላይ መውጣቷ በተለይ መይሄቷን የማንበብ እድል ላላገኙና ለአዲሱ ትውልድ በእጅጉ ጠቃሚ ነውና እንኳን ወደ ድረገጽ መጣችሁ እላለሁ፡፡
ReplyDelete