Thursday, December 15, 2011

ትዳር ለመመሥረት መሠረታዊ ጉዳዮች


                                   Read PDF                  
    በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 1፣ ላይ  የቀረበ
ወንዶች ወይም ሴቶች ትዳር ለመያዝ ሲፈልጉ በዕድሜ ለአካለ መጠን መድረስ አለባቸው፡፡ ሥጋዊ እድገት ብቻ ሳይሆን በመንፈስም መጐልመስና በአእምሮም መብሰል አስፈላጊ ነው፡፡
ለአካለ መጠን መድረሳችንን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ለአካለ መጠን መድረሳችንን ማወቅ የምንችለው ከዚህ በታች የተጻፉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ስንችል ነው፡፡

በውሳኔዬ ለመጽናት እችላለሁን?

አንድ ልጅ ኳስ ለመጫወት ቈርጦ ሳለ፥ ሌላ ልጅ ሲንሸራሸር ሲያይ መንሸርሸር ያምረዋል፤ ይኸው ልጅ ሌላ ልጅ ደግሞ ብይ ሲጫወት ሲያይ ብይ መጫወት ያምረዋል፡፡ ይህ በሁሉም ልጆች ላይ የሚታይ የልጅነት ጠባይ ነው፡፡ ለአካለ መጠን የደረሰ ሰው ግን ሐሳቡን ከመቊረጡ በፊት በጣም ያሰላስላል፤ ከቈረጠ በኋላ ግን መለወጥ በጣም አስፈላጊ ካልሆነበት በቀር አንዴ ያጸደቀውን ሐሳብ ያጸናል፡፡ ይህም የሐሳብ መጽናት የሚኖረው (ሊኖር የሚችለው) ራሳችንን ለመግዛት የቻልን እንደ ሆነ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕግሥተኛ ሰው ከኀያል ሰው ይሻላል፤ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስድ ይበልጣል  ይላል (ምሳ. 16፥32)

ኀላፊነትን ልቀበል የምችል ሰው ነኝን?

አንድ ሕፃን ችግር ሲያገኘው እንዲረዱት ወደ እናቱ ወይም ወደ አባቱ ይሮጣል፡፡ ለአካለ መጠን የደረሰ ሰው ግን ኀላፊነቱን ስለሚያውቅ በገዛ ራሱ ከችግሩ ለመውጣት ይሞክራል እንጂ ችግሩን እንዲፈቱለት ወደ ዘመዶቹ አይሮጥም፡፡ ይህን የሚያደርገው የሌሎችን ምክር በመናቁ አይደለም፤ ግን በቅድሚያ የራሱን ኀላፊነት መወጣት ስላለበት ነው፡፡ የሚጐዳውንና የሚጠቅመውን የማያውቅ ልጁ ጩቤንና ክብሪትን እንዲሁም ሌሎች የሚጐዱ ነገሮችን እንደ አሻንጉሊት አድርጐ ቢጫወትባቸው በራሱ ላይ አደጋ እንደሚያደርስ ሁሉ፥ የቤተ ሰብ አስተዳደር፥ የቤት አጠባበቅ፥ የዕቃ አያያዝና ይህን የመሳሰሉትን የኀላፊነት ሥራዎች ለመውሰድ ራሳቸውን ያላዘጋጁ ወጣቶች ትዳር ቢመሠርቱ ችግር እንጂ ደስታ አይኖራቸውም፡፡
ለዘመናዊ የቤተ ሰብ ኑሮ የሚረዷቸው ነገሮች ቢኖሯቸው እንኳ ያልተሰበ በሽታና ድኽነት ብዙ ቤተ ሰቦችን ስለሚያጠቃ እነዚህን ችግሮች በሕፃን አስተሳሰብ ሳይሆን በበሰለ አእምሮ በጸሎት በድፍረትና በብርታት መቋቋም ያስፈልጋል፡፡

የበደሉኝን ይቅር እላለሁን? የበደልኋቸውንስ?

በዚህ ዓለም ስንኖር ሳንበድልና ሳንበደል ለመኖር በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን ለአካለ መጠን የደረሰ ሰው ሲበድል ይቅርታን መጠየቅ እንዳለበት ያውቃል፡፡ በተበደለም ጊዜ ይቅርታ አድራጊ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የተጋቡ ወጣቶች ነበሩ፤ ሚስት ከጐረቤትዋ ጋር ስትጫወት ጊዜውን ሳታውቀው የምሳ ሰዓት ደርሶባት ሳትሰናዳ ባል ለምሳ ከተፍ አለ፤ እሷም ጥፋትዋን ዐውቃ ይቅርታ ጠየቀችው፤ እርሱም እውነተኛነትዋን ተረድቶ ፍቅሩን በይቅርታው ገለጸላት፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ እርሷ ጥሩ ምግብ አዘጋጅታ ቤትዋን አሳምራ ለራት ስትጠብቀው ሰዓት አሳልፎ፥ የተሠራው ቀዝቅዞ፥ ራሱም ሌላ ዘንድ ራት በልቶ ጠግቦ እያገሳ ያለወትሮው በሌሊት መጣ፡፡ እንደ መጣም ይቅርታ ሳይጠይቅ ተኛ፡፡ የዚህ ዐይነቱ ተግባር መልካም ነውን? አይደለም፡፡ “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተም ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” (ሉቃ. 6፥31)፡፡

ደስተኛ ሰው ነኝን?
ትዳር ለመያዝ ለሚፈልግ ሰው ሁሉ የራሱንና የትዳር ጓደኛውን ጠባይ መመርመር ይገባዋል፡፡ ራሱን የሚፈትነው ከዚህ በታች የሠፈሩትን ጥያቄዎች በመመለስ ይሆናል፡፡

ሀ. በጥፋትህ ብትወቀሥ ይከፋሃልን?
ለ. ዕቅድህ ባይሳካ ትቈጣለህን?
ሐ. በፍሬ ቢስ ነገር ቱግ ትላለህን?
መ. ያለ ምንም ምክንያት ትኰሳተራለህን?

ከዚህ በላይ በዐጭሩ የሰፈሩት ለኑሮ አደገኛ የሆኑ ነገሮች በሕይወታችሁ ውስጥ እንዳሉ እያወቃችሁ ሳታስወግዷቸው ትዳር አትመሥርቱ፤ ትዳር ብትመሠርቱ ግን የሚገጥማችሁ ችግር እንደ ሆነ ከዚሁ ልትረዱ ትችላላችሁ፡፡ አንድ ሰው ያለበትን ክፉ ዓመል ለመተው ቢፈልግ በእግዚአብሔር ኃይል ሊያስወግደው ይችላል፡፡
በሕይወታችሁ ስለ ተቀበላችሁት መልካም ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ፡፡

ሌላውን ሰው እንደ ራስህ ውደድ

ራሳችንን መውደድ ከሁሉ ቀላል ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ስለ ምቾታችን ስለ ወደ ፊቱ ኑሮአችን፥ ስለ ኀይላችን ስለ ኀዘናችንና ስለ ክብራችን እናስባለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ነገር ዐውቆ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ ብሎ”  አዘዘ (ማቴ. 22፥39)፡፡ ለእኔ ብቻ የማይል፥ ንፉግ ያልሆነ ሰው ስለ ሰዎች ስሜት በማሰብ ሊያደርጉለት እንደሚፈልግ ያደርግላቸዋል፡፡ ያለውን ነገርና ፍቅሩንም ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ ነው፡፡
መልካም የሆነ የክርስቲያን ቤተ ሰብ ለመመሥረት የሚችሉ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ራሱን ወዳድ የሆነ ሰው ግን ትዳር ቢመሠርትም አንዱ ላንዱ ችግር ፈጣሪ በመሆን ሥቃይና ሐዘን ያተርፋሉ፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ለሌሎች የሚያስቡ ሰዎች ከሆኑ በአንድነት ምንኛ ደስ ይላቸዋል!!

1 comment:

  1. ጮራዎች፦ እንደዚህ በብሎግ ወጥታችሁ የእግዚአብሔርን የቃሉን እውነት ለማካፈው በመነሳሳታችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ። ከያዛችሁት ግን ጠበቅ አድርጋችሁ ያዙት። ጽሑፎችን በየስንት ጊዜ እንደምትለጥፉ ለአንባቢያችሁ ንገሩ። ቃላችሁንም ጠብቃችሁ ጽሑፎችን ለጥፉ። በሳምንት ምንት አንድ ጊዜ ከሆነ የምትለጥፉት ሳታስታጉሉ ለጥፉ። ራዕያችሁን ደግሞ ለአንባብያን አሳውቁ። ያዝ ለቀቅ የምታደርጉ ከሆነ መተው ይሻላል። ይህን ሁሉ የምለው፤ ድረ ገጽ ከፍታችሁ መንቀሳቀስ መጀመራችሁ እጅት አስደስቶኛል ግን ያዝ ለቀቅ አይነት እንዳይሆን ደግሞ ፈራሁ።

    ReplyDelete