Saturday, December 31, 2011

ሰላማችን ክርስቶስ ነው

Read PDF
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ)
ዓለም ዛሬ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት በታላቅ ሥጋት ላይ ወድቃ ትሸበራለች፡፡ ድርቅና በረሓማነት የዓለምን ሕዝብ ለረኃብና ለበሽታ አጋልጦታል፡፡ ከዓለም ሕዝብ ከፊሉ ያህል በጐርፍ በረኃብ፥ በበሽታ፥  በመሬት መንቀጥቀጥና በዐውሎ ነፋስ ሕይወቱንና ንብረቱን እያጣ ነው፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፤ አንዱ መንግሥት ከሌላው በፖለቲካ፣ በድንበር እየተናቈረ፥ በንግድ ውድድር እየተጐናተለ፥ ጕልበተኛው መንግሥት ደካማውን እያጠቃ ነው፡፡ እንዲያውም የአንዳንድ አገር ሕዝብ እርስ በርሱ በጦርነት ሲተላለቅ ይታያል፡፡ ስለዚህም ነው “ሰላም! ሰላም!” የሚል ድምፅ በዓለማችን ዙሪያ በከፍተኛ ሁኔታ የሚስተጋባው፡፡


የርግቧ ሥዕል ከነወይራ ቀንበጧ በየጋዜጣው በየመጽሔቱና በየቅስቱ በሰፊው ተሥላ ትታያለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት መልእክተኞችም በየቦታው በአስታራቂነት ይሯሯጣሉ፡፡ ይህ በዚህና በዚያ የሚሰማው ጩኸት፥ የሚደረገው ሩጫና ግርግር የተከሠተውን ውጥረት በመጠኑ ለማርገብ እንጂ እውነተኛውን መሠረታዊ ሰላም ለማስፈን አልቻለም፡፡ እውነተኛውን ሰላምስ? መቼ፥ እንዴት ይገኝ ይሆን? የእግዚአብሔር ቃል ለዚህ መልስ አለው፡፡
“እርሱ ሰላማችን ነውና፥ ሁለቱን ያዋሐደ፤ በዐዋጅ የተነገሩትን የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፥ ይህም ከሁለታቸው አንድን ዐዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ፤ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡ መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምሥራች ብሎ ሰበከ፡፡ በእርሱም ሥራ በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና” ይላል፡፡ (ኤፌ. 2፥14-17፡፡)
ሰው ራሱን፣ መሰሎቹን ተፈጥሮንም ጭምር መጥላቱና መጕዳቱ፥ እንዲሁም በመሰሎቹና በተፈጥሮ፥ በራሱም ጭምር መጐዳቱ ከእግዚአብሔር ጋር የመጣላቱ ውጤት ነው፡፡ አሁንም ከእግዚአብሔር ጋር እንድንስማማና ሰላም እንዲኖረን ኢዮብም ይመክረናል (ኢዮብ 22፥21-30)፡፡
ስለሆነም ሰው ሁሉ እግዚአብሔር ባዘጋጀለት የዕርቅ መንገድ ከአምላክ ጋር ለመታረቅ ሥምረት (እሺ ባይነት) ቢኖረው “ሰላም በምድር” ይሆን ነበር፡፡ አሁንም ነገም “ሰላም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ፡፡”

No comments:

Post a Comment