Thursday, June 6, 2013

ርእሰ አንቀጽ


እግዚአብሔር አይዘበትበትም

ገበሬ በመኸር ሊሰበስብ የሚችለው ያንኑ የዘራውን ዐይነት አትርፎና አትረፍርፎ እንደ ሆነ ለማስገንዘብ፥ ያልዘራነውን እንሰበስባለን ብላችሁ በእግዚአብሔር አትቀልዱ፤ እግዚአብሔር ሊዘበትበት አይገባም ሲል የእግዚአብሔር መንፈስ በሐዋርያ ጳውሎስ በኩል አስተማረ (ገላ. 6፥7-9)፡፡ እየበቀለና እያደገ ለአዝመራ ደርሶ የምናጭደውና በትርፍ የምንሰበስበው ያንኑ የዘራነውን የእህል ዐይነት ነው፡፡ ጓያ የዘራ የስንዴ ምርት፥ ባቄላ የዘራም የጤፍ ምርት እግዚአብሔር ይሰጠኛል ብሎ አይጠብቅ፡፡ ነገ እንዲያገኝ የሚፈልገውን የምርት ዐይነት ካወቀ ለዚያ አዝመራ የሚያበቃውን ዘር ዛሬ መዝራት አለበት፡፡ ሌሎች ሰዎችም ሊያገኙ የማይችሉትን እንደሚያገኙ አስመስሎ ኢ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲደክሙ መምራት ለሁሉም እንደየሥራው የሚከፍል እግዚአብሔር ጻድቅ ፈራጅ የሆነበትን የቅድስናውን ባሕርይ የለወጠ አስመስሎ ማስተማር ነውና በእግዚአብሔር አንቀልድ፡፡ ይህ ዐይነቱ ተልእኮ መጥፎ ምርት ለመሰብሰብ የሚያበቃ መጥፎ ዘር መዝራት ነውና፡፡ ምድራዊ ዳኛ እንኳ ጸያፍና ነውር የሚለው፥ እንዲያውም የሚያፍርበት አድልዎኛነትና ፍርድን ማዛባት በእግዚአብሔር ዙፋናዊ ችሎት ይሠራበታል ከማለት የበለጠ ድፍረት ከቶ የለም፡፡ ስለዚህ በምኞታችንና በንግግራችን እውነቱን እውነት፥ ሐሰቱንም ሐሰት ነው እንበል፡፡ ይህን አለማለት በሰይጣን ጐራ መሰለፍ ነውና (ማቴ. 5፥37)፡፡

በአለቃ ስም ከሚነገሩ ቀልዶች መካከል አንዱን እዚህ ብንጠቅስ ተገቢ ስፍራው ይመስለናል፡፡ በርኩሳን መናፍስት አገልጋይነቱ ሰዎችን ሲያሳስት የኖረ ሰው ሞተ፡፡ ሥራውንና የደለበ ሀብቱን ቤተ ሰቡ ወረሰ፡፡ ወራሾቹም የኀጢአት ስርየት ይገዙለት ዘንድ ከዕለተ ሞቱ ጀምሮ በዐርባው፥ ከዚያም በኋላ በሰማኒያው፥ በመንፈቁና በየዓመቱ በከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ጸሎተ ፍትሐት አስደረጉለት፡፡ ከዐርባው ድግስ ተቋዳሾች መካከል አንዱ አለቃ ስለ ነበሩ፥ በአጠገባቸው ተቀምጦ ይመገብ የነበረ ሌላው አለቃን ጠየቃቸው፡፡ “ሟቹ ንስሓ አልገባም፤ ወራሾቹ ሀብቱን ወርሰዋል፤ ሥራውንም ቀጥለዋል፤ አሁን እኛ የጸሎታችን ዋጋ የሆነውን ድግስ የምንመገበው ለሟቹ ነፍስ ስርየት አሰጥተናል፤ ርግጠኞች ነን ብለን ነውን? ርግጠኛ ባልሆነ የስርየት ሽያጭስ አንጠየቅምን? ቢላቸው፤
“እኛ እንብላ እያልን ማራት ማራት፤
አምላክ ከፈለገ ገነት ይጨምራት፤
ካልፈለገም ደግሞ እንጦርጦስ(ሲዖል) ያውርዳት፡፡” በማለት መለሱለት ይባላል፡፡ በእውነት እንዲህ ተብሎ ከሆነ ኀላፊነት ከማይሰማው ኅሊና የመነጨ አነጋገር ነው፤ አያሥቅም፡፡


ሰዎች በሕይወተ ሥጋ በሚገኙበት ጊዜ ሊጓዙበትና ሊገቡበት ተገቢ የሆነውን ጠባብ በርና ቀጭን መንገድ በማመልከት ፈንታ ምን ጊዜም እውን ሊሆን በማይችል የሕልም ጐዳና መምራት፥ እንደ አለቃ አነጋገር ለእርድ እንስሳትን እንደ ማድለብ የሚቈጠር ዘዴ ሲሆን፥ በአመዛኙ ግን ጨካኝነት ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ጠማማው እንዲቀና፥ ሸካራው እንዲለሰልስ ተራራው እንዲናድ፥ ዐዘቀቱም እንዲሞላ መሰበክ ያለበት ዛሬ ነው፡፡ ስብከቱም በተሰባኪው ላይ ውጤት ማምጣት ያለበት አሁን ነው (2ቆሮ. 6፥2)፡፡

ክርስትና ነገሮች ሁሉ በብልጠት የሚቀለጣጠፉበት የሃይማኖት ክፍልና ጮሌ ወገኖች የሚጠቃቀሙበት ሥርዐት አይደለም፡፡ የምንለውን ለማስረዳት ስለ አንዲት ጮሌ ሴት በወንጌል የተጻፈውን ታሪክ እናስታውስ፡፡ “የተሸከመችህ ማሕፀን ብፅዕት ናት፤ የጠበሃቸው ጡቶችም ብፁዓት ናቸው፡፡” ስትል አካባቢውን አደባለቀችው በጊዜው ሴትየዋ “መልካም የተሰኘ ቅኔ አበረከትኩ፤ የጌታን  ሞገስ በብልጠቴ ገንዘብ አደረግሁ፤ ዛሬ በሐዋርያቱ መካከል ሹመት፥ ለነገውም ገነት የሚያስገባ የይለፍ ወረቀት በእጄ አስገባሁ” ሳትል እንዳልቀረች መገመት ይቻላል፡፡ ቢሳካ ኖሮ አቋራጭ መንገድ ይሏል ይህ ነበር፡፡ ከሰሚዎቹም መካከል “ምነው ይህ ዘዴ ቀደም ብሎ በተከሠተልኝና በተጠቀምሁበት! አዬ ጉድ ተቀደምኩ!” በማለት የተጸጸቱ አልታጡ ይሆናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለጮሌዪቱ አንጀቷን ብጥስ የሚያደርግ ቃል ነበረ የመለሰላት፡፡ በዚያ ዐይነቱ የተሳሳተ መንገድ ማንም እንዳይጓዝና እንዳይጠፋ በቅድሚያ የሚከላከልና የሚያስጠነቅቅም መልእክት ስለሆነ የመልሱ እንደዚያ ሆኖ መገኘት አስፈላጊነት ነበረው፡፡ ብፅዕና ከእርሱ ጋር በሥጋ በመዛመድ እንደማይገኝ ለመግለጽ “ብፁዓን፤ መባል የሚገባቸውስ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰሙና የሚጠብቁ ናቸው” አላት (ሉቃ. 11፥27-28)፡፡ ጌታችን የሴትዮዋን ንግግር በቸልታ፥ ወይም በፈገግታ ቢያልፈው ኖሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ጮሌዎች በሥጋ ዝምድና በኩል የሚንጠላጠሉበትና የሚጠለሉበት፥ የሚታጐሩበትና የሚጠቃቀሙበት ድርጅት በሆነ ነበር (ዘዳ. 10፥16-17)፡፡

ከዚህም በቀር ጌታችን ኢየሱስ ቃሉን በመቀበልና እንደ ቃሉም በመኖር ለሚገኝ መንፈሳዊ ዝምድና እንጂ ለሥጋ ዝምድና ከፍተኛ ስፍራ እንዳልሰጠ ወንጌላውያን ያረጋግጡልናል (ማቴ. 12፥46-50፤ ማር. 3፥31-35፤ ሉቃ. 8፥20-21፤ ዮሐ. 6፥63)፡፡ ለሥጋ ዘመዶቹም ቢሆን የተከፈተ በር ያለው ያው እንደ ሌሎቹ በቃሉ በኩል ከእርሱ ጋራ በመንፈስ ሲዛመዱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የቅድስት እናቱ ብፅዕና እንኳ የተመሠረተው በመልእክተኛው በኩል ከእግዚአብሔር የተነገራትን ቃል አምና መቀበሏ ነውና፡፡ “ወብፅዕት አንቲ እንተ ተአምኒ ከመ ይከውን ቃለ ዘነገሩኪ እም ኀበ እግዚአብሔር” እንዲል (ሉቃ. 1፥45)፡፡ ከዚህ የተነሣም የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ያደረባት እመቤት አምላኳና መድኀኒቷ ከሆነው ልጇ ጋር በመንፈሳዊ ዝምድና ለሚያስተሳስረው ቃል ትኵረት እንዲሰጡ ሰዎችን ስታሳስብ “እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለች፡፡


በሥጋ ዝምድና የሚሠራ ነገር አለመኖሩን ከልጇ መልስ አሰጣጥ ከተረዳች በኋላ ነበር እንዲህ ያለችው (ዮሐ. 2፥1-5)፡፡ እንደዚህ ከሆነም የዘራነውን መጥፎ ዘር እንዳንሰበሰብ የሚከላከልልን ኀይል ከቶ የለምና፤ ለነገ መልካም አዝመራ እንድንበቃ፥ በእግዚአብሔርና በዙፋናዊ ችሎቱ መቀለድን ትተን ዛሬ መልካሙን ዘር እንዝራ፡፡ እንደ ቃሉም እንኑር፡፡ እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን፡፡

በጮራ ቍጥር 7 ላይ የቀረበ

2 comments:

  1. እውነት ነው በቅንነትና በትህትና ዛሬ በጉብዝናችን ወራት ያልፈለግነው እግዚአብሔር ነገ እኛ ካለፍን በኋላ በሀብታም ዘመዶቻችን ወይንም ተበድረው ተለቅተው 40 እና 80 ለማውጣት በሚጣጣሩት በኩል እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ዝምድና ማግኘት አይቻልም ስለዚህ ሳይመሸ በጊዜ ወደ እርሱ መቅርብ በልጁ በኩል የተሰጠንን የተስፋ ህይወት በእለት ተእለት ሕይወታችን እየተቋደስን እርሱን ለመምሰል እየተጋን መኖር ጌታ በፀጋው ይርዳን አሜን

    ReplyDelete
  2. እውነት ነው በቅንነትና በትህትና ዛሬ በጉብዝናችን ወራት ያልፈለግነው እግዚአብሔር ነገ እኛ ካለፍን በኋላ በሀብታም ዘመዶቻችን ወይንም ተበድረው ተለቅተው 40 እና 80 ለማውጣት በሚጣጣሩት በኩል እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ዝምድና ማግኘት አይቻልም ስለዚህ ሳይመሸ በጊዜ ወደ እርሱ መቅርብ በልጁ በኩል የተሰጠንን የተስፋ ህይወት በእለት ተእለት ሕይወታችን እየተቋደስን እርሱን ለመምሰል እየተጋን መኖር ጌታ በፀጋው ይርዳን አሜን

    ReplyDelete